ወላይታ ድቻ ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

በርካታ ዝውውሮችን የፈፀመው ወላይታ ድቻ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በነሐሴ አጋማሽ ይጀምራል፡፡

በ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ሁለት መልክ ከነበራቸው ክለቦች መካከል አንዱ ወላይታ ድቻ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አጀማመሩ እጅግ ደካማ የነበረው እና ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ሹመት በኃላ እጅጉን በተሻሻለ መልኩ ዓመቱን ያገባደደው ክለቡ ለቀጣዩ የ2014 የውድድር ዓመት ምንም እንኳን ወሳኝ ተጫዋቾቹን ቢያጣም አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርምን በመቅጠር፣ ውል በማራዘም እና የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር በመፈፀም ተጠምዷል፡፡

ክለቡ የሰባት ተጫዋቾችን ውል ሲያድስ ስምንት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን አሳድጓል። ፅዮን መርዕድ፣ ወንድወሰን አሸናፊ፣ ዘካሪያስ ቱጂ፣ ንጋቱ ገብረሥላሴ፣ ቃልኪዳን ዘላለም፣ ሀብታሙ ንጉሤ፣ አዲስ ህንፃ፣ ምንይሉ ወንድሙ፣ ፍሰሀ ቶማስ እና በረከት ወልደዮሐንስን ደግሞ ወደ ስብስቡ መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም አዳዲስ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም የሚጠበቀው ወላይታ ድቻ ከነሐሴ 17 ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እንደሚጀምር የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ሳሙኤል ለሶከር ኢትዮጵያ ጠቁመዋል፡፡

ያጋሩ