የከፍተኛ ሊጉ ተሳታፊዎች ቁጥር እና ወራጅ ክለቦች እጣ ፈንታ በቅርቡ ውሳኔ ያገኛል

የተሳታፊ ቁጥር መፋለስ ያጋጠመው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በቀጣዩ ዓመት በምን መልኩ ይካሄዳል፣ በ2013 የውድድር ዘመን ወደ አንደኛ ሊግ ወርደው የነበሩ ክለቦችስ በከፍተኛ ሊጉ ይቀጥላሉ ወይንስ አይቀጥሉም የሚለው ጉዳይ በቅርቡ እልባት ያገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሦስት ምድቦች ተከፍሎ የ2013 የውድድር ዘመን ሲደረግ ቆይቶ መከላከያ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማን ወደ 2014 ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሳልፎ በተመሳሳይ ከሦስቱም ምድቦች የመጨረሻውን ሁለት ደረጃዎችን የያዙ ስድስት ክለቦች (ከምድብ ሀ ወሎ ኮምቦልቻ እና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን፣ ከምድብ ለ ካፋ ቡና እና አቃቂ ቃሊቲ፣ ከምድብ ሐ ደግሞ ከምባታ ሺንሺቾ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ) ወደ አንደኛ ሊጉ አውርዶ መጠናቀቁ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

መከላከያ ቻምፒዮን በሆነበት ምድብ ሀ ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች ደደቢት፣ አክሱም ከተማ እና ሶሎዳ ዓድዋ በትግራይ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር የተነሳ አስራ ሁለት ቡድኖች መወዳደር ሲገባቸው በዘጠኝ ክለቦች መካከል ሊደረግ እንደቻለም ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም የትግራይ ክልል ክለቦች በ2014 የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉም ሆነ ከፍተኛ ሊጉ የማይሳተፉ በመሆናቸው ምክንያት ከፕሪምየር ሊጉ የሚወርድ ቡድን የማይኖር መሆኑን ተከትሎ ከዚህ ቀደም 36 ክለቦችን ሲያሳትፍ የነበረው ውድድር ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥር ወደ 30 ዝቅ የሚል ይሆናል።

ይህን መነሻ በማድረግ እነዚህን ስድስት ክለቦች (ሦስት በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የነበሩት የትግራይ ክልል ክለቦች እና ሦስት ክለቦች ከፕሪምየር ሊግ የወረደ ባለመኖሩ) በቀጣዩ ዓመት ለመተካት የወረዱት ስድስት ክለቦች ልክ በቅርቡ እንደተደረገው የማሟያ ጨዋታ ለእኛም ይደረግልን እና ክለቦች ይለዩ የሚሉ ሀሳብ በተደጋጋሚ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ባገኘነው መረጃ መሠረት የወረዱ ክለቦች በድጋሚ እንደማይመለሱና በወረዱበት አንደኛ ሊግ በቀጣዩ ዓመት እንደሚወዳደሩ የሰማን ቢሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ከሆነ የወረዱት ስድስቱ ክለቦች ይቀጥሉ ወይንስ የመለያ ጨዋታ ተደርጎ ተሳታፊ ክለቦች ተለይተው ይታወቁ የሚለውን ጉዳይ ለማሳወቅ በቅርቡ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አካላት ተሰብስበው በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፉ እና አዲስ ነገር ሊኖር እንደሚችልም ፀሃፊው ነግረውናል፡፡

ከከፍተኛ ሊጉ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በአዳማ ከተማ በተደረገ የአንደኛ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ስድስት ቡድኖች ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማደጋቸው ይታወሳል፡፡