አቡበከር ናስር ዛሬ ማለዳ ወደ አዳማ አቅንቷል

ከብሔራዊ ቡድን አጋሮቹ ጋር ወደ አዳማ ሳያቀና ቀርቶ የነበረው አጥቂ ዛሬ ረፋድ ወደ ስፍራው ማምራቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኳታር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን በቅርቡ ማድረግ እንደሚጀምር ይታወቃል። በተለይ ከጋና እና ዚምቡዋቤ ጋር ላሉበት ቀዳሚ ጨዋታዎች ከቀናት በፊት ዝግጅት የጀመረው ቡድኑም ወደ አዳማ ሲያቀና አቡበከር ናስርን ሳይዝ እንደሆነ ዘግበን ነበር።

ሰኞ ከስብስቡ ጋር የኮቪድ-19 ምርመራ አድርጎ የነበረው አቡበከር ከግል ጉዳይ ጋር በተያያዘ የብሔራዊ ቡድኑን አሠልጣኝ ለሦስት ቀን ፍቃድ ጠይቆ ነበር። ተጫዋቹ አዲስ አበባ የነበረውን ጉዳይ ትናንት መስመር ካስያዘ በኋላም ዛሬ ማለዳ ወደ አዳማ በማቅናት ብሔራዊ ቡድኑን እንደተቀላቀለ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ተጫዋቹ ዛሬ በሚኖረው የቡድኑ ልምምድ ላይም ተሳታፊ እንደሚሆን ሰምተናል።

ያጋሩ