የጅቡቲ እና የኤርትራ ብሔራዊ ቡድኖች ልምምዳቸውን አከናውነዋል

ለ2022 የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚጫወቱት የጅቡቲ እና የኤርትራ ብሔራዊ ቡድኖች ልምምዳቸውን ሰርተዋል።

በኮስታሪካ አዘጋጅነት የ2022 የዓለም ከ20 ሴቶች ዋንጫ ይደረጋል፡፡ ለዚህም ውድድር በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ሀገራት የቅድመ ማጣሪያ መርሀግብራቸውን በዚህ ሳምንት ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ ከእነኚህ መካከል የጅቡቲ እና የኤርትራ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ይገኝበታል፡፡ በሁለቱ መካከል ባለው ችግር የተነሳ በጅቡቲ መደረግ የነበረበት ይህ ጨዋታ ካፍ በገለልተኛ ሜዳ መደረግ አለበት ባለው መሠረት ዕሁድ በ10፡00 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ፡፡

ከትናንት በስቲያ ወደ ኢትዮጵያ 28 የልዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ የመጣው የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን በአዘማን ሆቴል ማረፊያውን ካደረገ በኋላ በትናንትናው ዕለት 10 ሰዓት ላይ የመጀመሪያውን ልምምድ ማከናወኑ ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዕለትም ቡድኑ ከ9 ሰአት ጀምሮ ለአንድ ሰዓት የቆየ የሁለተኛ ቀን ልምምዱን ሰርቷል።

እንደ ኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ሁሉ ለዚህ ጨዋታ በትላናትናው ዕለት ሐሙስ ከ25 በላይ ልዑኩን ይዞ ምሽት 4 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ የደረሰው የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ያረፈ ሲሆን በዛሬው ዕለት ጠዋት 12 ሰዓት ባለፈበት ሆቴል መጠነኛ የአካል ብቃት ልምምድን ከሰራ በኋላ ከሰአት ከ10 እስከ 11 ሰዓት የቆየ ልምምዳቸውን ጨዋታ በሚያደርጉበት አበበ ቢቂላ ስታዲየም መስራታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ተገንዝባለች፡፡

ነገ አመሻሽ ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች የመጨረሻ ልምምዳቸውን የሚሰሩ ሲሆን ዕሁድ 10፡00 ላይ ደግሞ ማጣሪያቸውን ይከውናሉ፡፡ ይህን ጨዋታ በዋና እና በረዳት ዳኝነት ከሩዋንዳ አራተኛ ዳኛ ደግሞ ከኬኒያ እንዲመሩ መመረጣቸውንም ለማወቅ ቸለናል፡፡