አዲስ አበባ ላይ የተደረገው የኤርትራ እና ጂቡቲ ጨዋታ ኤርትራን አሸናፊ አድርጓል

የኤርትራ እና ጂቡቲ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድኖች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ በኤርትራ የበላይነት ተጠናቋል።

በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ላይ ለማለፍ የአፍሪካ ሀገራት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ማድረግ ጀምረዋል። ከእነዚህ የማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል ደግሞ በገለልተኛ ሜዳ እንዲካሄድ ፊፋ የወሰነው የኤርትራ እና ጂቡቲ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ይገኝበታል። የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታም ዛሬ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተደርጓል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የኤርትራ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ አብርሃም ተገኝተው በተመለከቱት ግጥሚያ ላይ ኤርትራዎች ተሽለው ሲንቀሳቀሱ ጂቡቲዎች ደግሞ ተዳክመው ታይተዋል።

ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ጂቡቲዎች የግብ ክልል በቀላሉ መድረስ የያዙት ኤርትራዎች በፈጣን የኳስ ቅብብሎቻቸው ግቦችን ለማግኘት መታተር ጀምረዋል። በተለይ ዲያና እስቲፋኖስ እና ደሊና ሳህሌ የጂቡቲ ተከላካዮች የራስ ምታት ሆነው ታይተዋል። 

ጨዋታው 13ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም 13 ቁጥር ለባሿ ደሊና ሳህሌ ከተከላካዮች አፈትልካ በመውጣት ኳስ እና መረብን አገናኝታ ቡድኗን መሪ አድርጋለች። ግቡ ባለቤት ደሊና በ27ኛው ደቂቃም ግቡን ባስቆጠረችበን እንቅስቃሴ ሌላ ያለቀለት እና ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ያገናኛትን ዕድል አግኝታ ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

በጨዋታው እጅግ ተዳክመው የታዩት ጂቡቲዎች በጀብደኝነት ተከላካዮቻቸውን ወደ መሐል ሜዳው አስጠግተው ለመጫወት ቢጥሩም አጨዋወታቸው ከጥቅም ይልቅ ጉዳት ይዞባቸው መጥቷል። በተለይ የቡድኑ ከኳስ ውጪ ያለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ድክመት ኖረበት ታይቷል። ቡድኑም በአጋማሹ አንድም የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጥር እጁን ለኤርትራ ሰጥቶ ወጥቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው አንድ ደቂቃ ላይ ከጥሩ ቦታ የቅጣት ምት ያገኙት ኤርትራዎች አጋጣሚውን መሪነታቸውን ለማስፋት ተጠቅመውበታል። በዚህም የተሰጠውን የቅጣት ምት ራህዋ ነጋ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይራው ኤርትራ ሁለት ለምንም መምራት ጀምራለች።

ከእረፍት መልስም የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የቀጠሉት ኤርትራዎች አጋማሹ በተጀመረ በ10 ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት እጅግ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን ፈጥረው ነበር። ነገርግን ሦስቱም አጋጣሚዎች መጨረሻቸው መረብ ሳይሆን ቀርቷል። በአንፃሩ ተጫዋቾችን አከታትለው በመለወጥ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ጂቡቲዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በመጠኑ ሻል ብለው ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል።

ዝናብ ማስተናገድ የጀመረው ጨዋታው 63ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ ዒላማውን የጠበቃ ሙከራ ያደረጉት ጂቡቲዎች በሌርማን ሲኪህ አማካኝነት ድንቅ ጎል ከወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ አስቆጥረዋል። ለተቆጠረባቸው ጎል ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ጊዜ ያላጠፉት ኤርትራዎች ደግሞ በደቂቃ ልዩነት በደሊና ሳህሌ አማካኝነት ዳግም መሪነታቸውን አስፍተዋል። 

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች እምብዛም ሳቢ ሳይሆን ከግብ ሙከራዎች ርቆ መደረግ ቀጥሏል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኤርትራዎች ከቆሙ ኳሶች እና ከመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ቢታትሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጨዋታውም በኤርትራ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ በተመሳሳይ እዚሁ አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የፊታችን ረቡዕ የሚደረግ ይሆናል።

ያጋሩ