ሲዳማ ቡና ስድስት ተጫዋቾችን አሳድጓል

በዝውውር ገበያው በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ሲዳማ ቡና ስድስት ወጣት ተጫዋቾችን ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ አሳድጓል፡፡

ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመጀመር ካሰበበት ነሀሴ 6 በተለያዩ ምክንያቶች በአራት ቀናቶች ገፍቶ በዛሬው ዕለት ሰኞ ነሐሴ 10 ልምምድ የጀመረው ሲዳማ ቡና በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ያመጣ ሲሆን ሦስት ውላቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾችን ለተጨማሪ ዓመት አድሶ በአንፃሩ ውል ከነበራቸው አራት ተጫዋቾች ጋር በስምምነት መለያየቱን በተለያዩ ጊዜያት በዘገባችን ገልፀን እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች በተጨማሪ በቀድሞው የክለቡ የግራ መስመር ተከላካይ ወንድማገኝ ተሾመ ከሚሰለጥነው ከ20 ዓመት ቡድኑ ስድስት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ማሳደጋቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በግብ ጠባቂነት ሀብታሙ መርመራ ፣ በተከላካይነት መኳንንት ካሣ፣ በመስመር አጥቂነት ማርኮ ተሾመ፣ ደግፈኝ ዓለሙ እና አቤኔዘር አሸናፊ እንዲሁም በተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ አልማው አሸናፊ ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ከ20 ዓመት ቡድን አሰልጣኝ የሆነው ወንድማገኝ ተሾመ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ረዳት ለመሆን መቃረቡን ሰምተናል፡፡