በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ለፍፃሜ የደረሱ ክለቦች ታውቀዋል

በዛሬው ዕለት በተደረጉ ሁለት የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ምስራቅ ክፍለከተማ እና ዱራሜ ከተማን ለፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

(በብሩክ ሀንቻቻ)

ወደ 2014 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር ላይ ለማለፍ ከሐምሌ 18 ጀምሮ በአርባ ስድስት ክለቦች መካከል በአስራ አንድ ምድቦች ተከፍሎ ሲደረግ በቆየው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ቀደም ብሎ አስራ ሁለት ክለቦችን ወደ አንደኛ ሊጉ መግባታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ለዋንጫ ለማለፍ ሁለት መርሀግብሮች በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ላይ ተደርገው ለፍፃሜ ያለፉን ለይቷል፡፡

3:00 ሲል የመጀመሪያው ጨዋታ የጋምቤላው አብይ አካዳሚ እና በምስራቅ ክፍለከተማ መካከል የተደረገ ነበር፡፡ ምስራቅ ክፍለከተማዎች ገና በጊዜ በአቡቲ ዋና ጎል መሪ የነበሩ ቢሆንም የምስራቁ ግብ ጠባቂ ተስፋሚካኤል በጋምቤላ አብይ አካዳሚዉ አጥቂ ላይ በሳጥን ውስጥ በሰራዉ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ከመረብ በማሳረፍ መደበኛዉ የጨዋታዉ ክፍለ ግዜ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል። በተሰጠው የመለያ ምት የሲዳማ ክልሉ ምስራቅ ክፍለከተማ 3-1 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ለዋንጫ ፍፃሜ ማለፉን አረጋግጧል።

በማስከተል 5:00 ሲል ቡሳ ከተማን ከዱራሜ ከተማ አገናኝቷል፡፡ የዱራሜ ከተማ የበላይነት በተንፀባረቀበት በዚህ ጨዋታ 2-0 በሆነ ዉጤት ዱራሜዎች ድል አድርገው ለፍፃሜው በቅተዋል። በጨዋታዉ የመጀመሪያ ደቂቃዎች በፍቃዱ መናሞ እና ኃይሌ ዓለሙ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ነው ዱራሜ ከተማዎች አሸናፊ መሆን የቻሉት፡፡

የፊታችን ሀሙስ ነሀሴ 13 በሚደረጉ የደረጃ እና የዋንጫ ጨዋታዎች የክልል ክለቦች ሻምፒዮናው ይጠናቀቃል፡፡ ለደረጃ አብይ አካዳሚ ከ ቡሳ ከተማ ጠዋት 3:00 ለዋንጫዉ ደግሞ 5:00 ሲል ምስራቅ ክፍለ ከተማ ከ ዱራሜ ከተማ ጋር መርሀግብራቸውን ይከውናሉ፡፡