የሙጂብ ቃሲም ዝውውር ጉዳይ በይደር ይታያል

ሙጂብ ቃሲም ዛሬ ወደ ድሬዳዋ ሊያጠናቅቅ የነበረው ዝውውር ወደ ነገ ተሻግሯል። 

የዛሬው ርዕሰ ዜና በመሆን መነጋገሪያ ሆኖ የዋለው ሙጂብ ቃሲም ወደ አልጄርያ ክለብ የሚያደርገው ዝውውር አለመሳካቱን ተከትሎ ወደ በሀገር ውስጥ አዲስ ክለብ እንደሚቀላቀል መናገሩን ረፋድ ላይ ገልፀን ነበር። በሌላ በኩል የፋሲል ከነማ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ብርሀኑ አጥቂው ወደ ውጭ የሚያደርገው ጉዞ የማይሳካ ከሆነ ተመልሶ ፋሲል ለመጫወት ህጋዊ ስምምነት የፈፀመ በመሆኑ ወደ ክለባችን ይመለሳል በማለት መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በሁለቱ ወገኖች ያለው ልዩነት ወዴት ያደርሳቸዋል የሚለውን ጉዳይ በጉጉት እየጠበቅን ባለንበት ሰዓት ሙጂብ ቃሲም፣ ወኪሉ እና አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ እንዲሁም የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ በጋራ በመሆን ከሰዓት በኋላ ወደ ፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ጎራ በማለት ሙጂብን ለድሬዳዋ ፊርማውን እንዲያኖር ታስቦ ነበር።

ይሁን እንጂ ያልጠበቁት ክስተት ተፈጥሯል። ፌዴሬሽኑ ሠራተኞች ይህን ጉዳይ እንደማያስተናግዱ እና የበላይ አካላት ነገ ቢሮ ሲገቡ ረፋድ አራት ሰዓት እንዲመጡ ትዕዛዝ በመስጠታቸው የተነሳ ሙጂብ ወደ ድሬዳዋ የሚያደርገው ዝውውር እክል ገጥሞታል።

የፌዴሬሸኑ ፕሬዝዳንት እና ዋና ፀሐፊ ከካሜሩን መልስ ለክልል ክለቦች ሻምፒዮና ፍፃሜ ሀዋሳ የሚገኙ ሲሆን ምን አልባት ነገ ሲመለሱ ለጉዳዩ መፍትሔ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ጉዳይ የሚኖሩ አዳዲስ ጉዳዮችንም እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።