የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮና ውድድር የተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር ዝቅ ብሎ እሁድ በባቱ ከተማ መካሄድ ይጀምራል።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ለመጀመርያ ጊዜ የከተማ አስተዳደር እና የክልል ከተሞች እንዲሁም የፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች በጋራ የሚሳተፉበት ከ17 ዓመት በታች ውድድር እሁድ በይፋ በባቱ ከተማ የሚጀመር ይሆናል። ከሳምንት በፊት በጁፒተር ሆቴል በተካሄደ የዕጣ ማውጣት እና የውድድር ደንብን አስመልክቶ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ 20 ቡድኖች እንደሚሳተፉ ተረጋግጦ በአምስት ምድብ የተከፈ የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ተከነውኖ ነበር። ሆኖም እሁድ በባቱ ከተማ በሚጀመረው ውድድር ለጊዜው ባልተገለፀ ምክንያት አማራ ክልል፣ አፋር ክልል፣ ቤኒሻንጉል ክልል እና ሰበታ ከተማ እንደማይሳተፉ ተረጋግጧል።
የተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር በማነሱ እና ተጨማሪ በውድድሩ ዙርያ በተመለከተ የክለቦች ተወካይ በተገኙበት ዛሬ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ በባቱ ከተማ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ውይይት ተካሂዷል። ፌዴሬሽኑን በመወከል የውድድር ዳሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ፣ ምክትል ፀሐፊው አቶ ሰለሞን ገብረ ሥላሴ እና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲያምረኝ ዳኜ በመሩት በዚህ ስብሰባ ከMRI እና ከኮቪድ ጋር እንዲሁም በውድድሩ ደንቦች ዙርያ የተለያዩ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል።
በመጨረሻም ባልመጡት አራቱ ክለቦች ምትክ የምድብ ድልድሉ አንደ አዲስ ማሸጋሸግ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ከተሟላው የምድብ ሀ እና ሐ ውጭ በድጋሚ እሁድ ዘጠኝ ሰዓት ሌላ የዕጣ ማውጣት ስራ እንደሚሰራ እና ምድቡ ወደ አራት ዝቅ እንደሚል ተነግሯል። ውድድሩም አስቀድሞ ነሐሴ 15 እንደሚጀመር ቢገለፅም አንድ ቀን ተገፍቶ እሁድ እንዲጀመርምተወስኗል። በዚህም መሠረት እሁድ ነሐሴ 16 ቀን የመክፈቻ ጨዋታ ሲደረግ 3:00 ላይ አዳማ ከተማ ከ ጋምቤላ ክልል፣ 5:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከ ከኦሮሚያ ክልል ይጫወታሉ።
እሁድ ጠቅለል ያለ የውድድር መርሐግብር ሲወጣ ሙሉ መረጃውን የምናደርሳቹ ይሆናል።