የዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ዕውነታዎች

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫው ተሳትፎ እና በቀጣይ ስለሚገጥማቸው የምድብ ቡድኖች ዕውነታ ተከታዩን ጥንክር አዘጋጅተናል።

33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በቀጣይ ዓመት በካሜሩን አስተናጋጅነት እንደሚከናወን ይታወቃል። የውድድሩ የምድብ ድልድልም ከደቂቃዎች በፊት በካሜሩን ያውንዴ በደማቅ ሥነ-ስርዓት ወጥቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቬርድ ጋር መደልደሉ እርግጥ ሆኗል። ሶከር ኢትዮጵያም ዋልያው በምድብ ከሚገጥማቸው ቡድኖች ጋር እንዲሁም በአፍሪካ ዋንጫው ያለው ታሪካዊ እውነታ እንደሚከተለው አዘጋጅታዋለች።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እስካሁን በ11 የአህጉሩ ትልቁ የሀገራት ውድድር (የአፍሪካ ዋንጫ) ላይ ተሳትፏል። ቡድኑ ከተሳተፈባቸው ውድድሮች አንድ (1962) ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ችሏል።

– ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር የተመለሰው ቡድኑም እስካሁን 27 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን አድርጓል። ቡድኑ ካከናወናቸው 27 ጨዋታዎች ሰባቱን ሲያሸንፍ በሦስቱ አቻ ወጥቶ በአስራ ሰባቱ ሽንፈት አስተናግዷል።

– ከላይ በጠቀስናቸው 27 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ብሔራዊ ቡድኑ 29 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ሲያስቆጥር በተቃራኒው 61 ግቦችን አስተናግዷል።

– በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ከካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቬርድ ጋር የተደለደለው ዋልያው ከዚህ ቀደም ከካሜሩን ጋር በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ተገናኝቶ ያውቃል። በ1970 በሱዳን አስተናጋጅነት በተከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የተገናኙት ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በጨዋታው አምስት ግቦችን በድምሩ አስቆጥረው ነበር። ጨዋታውም በካሜሩን 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

– ከካሜሩን በተጨማሪ በምድቡ ቡርኪና ፋሶን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቡድኑ ጋር በውድድሩ አንድ ጊዜ ተገናኝቷል። ዋልያው ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፈበት የ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይም ቡርኪና ፋሶ አራት ለምንም አሸንፋ ነበር።

– ኢትዮጵያ በተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሯ ቡርኪና ፋሶን በአንድ ምድብ አግኝታለች። ይህ ሲከሰትም ለስድስተኛ ጊዜ ሆኗል። ከዚህ ቀደም ዋልያዎቹ ከዛምቢያ እና ናይጄርያ (1982 እና 2013)፣ አይቮሪኮስት (1968 እና 1970) ፣ ቱኒዚያ (1962፣ 1963 እና 1965) እንዲሁም ግብፅን (1957፣ 1959፣ 1962 እና 1963) በተከታታይ ውድድሮቿ አግኝታለች።

– በአፍሪካ ዋንጫው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኬፕ ቬርድ ብሔራዊ ቡድን ሲገናኙ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

– ለ11ኛ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ ለ5ኛ ጊዜ ከአስተናጋጅ ሀገር ጋር ተደልድላለች። በ1959 (ግብፅ)፣ 1963 (ጋና)፣ 1965 (ቱኒዚያ) እና 1970 (ሱዳን) ከአስተናጋጆቹ ጋር በአንድ ምድብ ስትደለደል አሁን ደግሞ ከካሜሩን ጋር በአንድ ምድብ ተገኝታለች።