የድሬዳዋ ስታዲየም ተገምግሟል

የቀጣይ ዓመት የሊጉ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ጥያቄ የቀረቡ ከተሞችን መመልከት የቀጠለው የሊጉ የበላይ አካል ትናንት ደግሞ ወደ ድሬዳዋ አቅንቷል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የ2014 የሊጉን ውድድር ማስተናገድ የሚፈልጉ ከተሞች ጥያቄ እንዲያቀርቡ መጠየቁ ይታወሳል። ይህንን ዕድል በመጠቀምም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ስታዲየሞች ውድድሩን ለማስተናገድ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን ማኅበሩም የስታዲየሞቹን የማስተናገድ አቅም እና ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ተያያዥ ጉዳዮችን ለመመልከት ወደ ከተሞቹ ጉዞ ማድረግ ጀምሯል።

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀዋሳ እንዲሁም አዳማ በማቅናት የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ እና የአዳማ ሳይንስ እና ዩኒቨርስቲ ስታዲየሞችን የገመገመው አክሲዮን ማኅበሩም ትናንት ሦስተኛ ምልከታውን ለማድረግ ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል ድሬዳዋ አምርቶ ነበር።

ከአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ አመራሮች፣ ከጽሕፈት ቤት እና ከሊግ ኮሚቴው ተወጣትቶ የተዋቀረው ኮሚቴውም ትናንት ረፋድ ላይ የልምምድ ሜዳዎችን እና ሆቴሎችን ተመልክቷል። ኮሚቴው በምልከታውም የልምምድ ሜዳዎች ምቹ እንዲደረጉ የጠቆመ ሲሆን ሆቴሎችም ለስፖርተኞች ተስማሚ እንዲሆን መደረግ እንዳለበት ሀሳብ አንስቷል።

ከሰዓት ደግሞ ኮሚቴው ዋና ስታዲየሙን መጎብኘቱ ታውቋል። ከቀትር በኋላ በነበረው ምልከታም የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር መገኘታቸው ተመላክቷል። ምክትል ከንቲባውም የሚሰጣቸውን ግብዓቶች አስተካክለው የቀጣይ ዓመት ውድድርንም ከተማዋ እንድታስተናግድ እንደሚጣር መናገራቸውን የድሬዳዋ ከተማ የስፖርት ክለብ ማኅበራዊ ገፅ አስታውቋል።

ዛሬ ከድሬዳዋ የሚነሳው ልዑኩም ነገ የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየምን ለመመልከት ጉዞ እንደሚያደርግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።