ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መመለሱን ያረጋገጠው መከላከያ የ2014 የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ቢሾፍቱ ከተማ ላይ ጀምሯል፡፡
የ2013 የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ሻምፒዮን በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በድጋሚ መመለሱን ያረጋገጠው መከላከያ ለቀጣዩ የ2014 የውድድር ዘመን ተጠናክሮ ለመቅረብ የአሠልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌ እና ረዳቱ ዮርዳኖስ አባይን ውል በማደስ እንዲሁም ደግሞ ሁለት ተጨማሪ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት በመጨመር ቀጥሎም ወደ ዝውውር ገበያ ጎራ በማለት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የነባሮችን ውል በማደስ ያለፉትን ወራት ቆይታ አድርጓል፡፡ በተጠቀሱት እንቅስቃሴዎ ተጠምዶ የከረመው ቡድኑም በዛሬው ዕለት ወደ ቢሾፍቱ ከተማ በማቅናት በመከላከል ኮሌጅ በሚገኘው ሜዳ ዝግጅቱን ረፋድ ላይ በይፋ ጀምሯል፡፡
በማርካን ሎጅ ማረፊያውን ያደረገው ክለቡ ቀጣዮቹ የልምምድ መርሐ-ግብሮቹን እዛው ቢሾፍቱ እየሰራ እንደሚቆይ ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች፡፡