ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ትልቁ አህጉራዊ ውድድር የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ተጋጣሚዎቹን አውቋል።
በቀጣይ ዓመት በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማለፉ ይታወቃል። 24 ተሳታፊዎች ያሉበት ትልቁ የአህጉሩ ሀገራት ውድድር ከጥር 1 – 29 (ጃኑዋሪ 9 – ፌብሩዋሪ 6) ድረስ የሚደረግ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ የምድብ ድልድሉ በደመቀ ሁኔታ በካሜሩን ወጥቷል።
ከሦስት ሰዓት ጀምሮ በያውንዴ ሴንተር በተካሄደው የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ላይ የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪክ ሙሴፔን (ዶ/ር) ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የእግርኳስ ፌዴሬሽን የበላይ አመራሮች፣ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። የካፍ የውድድር ዳይሬክተር ሳምሶን አዳሙ አንጋፋዎቹን የቀድሞ ተጫዋቾች ሳሙኤል ኢቶ፣ ጋዬል ኢንጋናሙቲ፣ ራባህ ማጄር፣ ዲዲየር ድሮግባ እና አሳሙዋ ጂያንን እየመራ በውድድሩ የሚሳተፉ 24 ሀገራት አራት አራት ሆነው በስድስት ምድብ እንዲደለደሉ አድርጓል።
አይቮሪኮስትን ተከትሎ በምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች የአፍሪካ ዋንጫ ትኬቱን የቆረጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከደቂቃዎች በፊት በወጣው ድልድል በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ኬፕ ቨርዴ እና ቡርኪና ፋሶ ጋር መደልደሉ ታውቋል።
የውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታም በካሜሩን እና ቡርኪና ፋሶ መካከል ሲደረግ በዚሁ ምድብ የምገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ የውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከኬፕ ቨርዴ ጋር ያደርጋል።