እስካሁን ለቀጣዩ ዓመት እንቅስቃሴ ያልጀመረው የመዲናይቱ ክለብ አዲስ ቦርድ ያቋቋመ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜም ቦርዱ የአሰልጣኙ የመቀጠል እና ያለመቀጠል ዙርያ ጨምሮ ሌሎች ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ቀጠሮ ይዟል፡፡
በቅርቡ ሶከር ኢትዮጵያ በዘገባዋ አዲስ አዳጊው ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ለ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እያደረገ ያለው የተጫዋቾች ዝውውርም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈ ባለመሆኑ ክለቡ ምን እየሰራ ይገኛል ? በሚል ለክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ታከለ እና ለክለቡ አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጥያቄ አቅርበን እንደነበር አይዘነጋም። የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት “ከበጀት ጋር ማለቅ ያለባቸው ጉዳዮች ስላሉ እነሱን አጥብቀን እየሰራን እንገኛለን። ተጫዋቾችን በተመለከተ አሰልጣኙ እንዲሰራ አዘነዋል።” በማለት መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡ አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር በበኩሉ “ክለቡ ለእኔ ምንም አይነት ነገር አላዘዘኝም” በማለት የክለቡ ስራ አስኪያጅ የሰጡትን ምላሽ ማስተባበሉንም ዘግበን ነበር፡፡ ክለቡም ከሰሞኑ ባደረጋቸው ተደጋጋሚ ስብሰባቸው ክለቡ ያለበትን የፋይናንስ ችግር በፍጥነት ቀርፎ በጀት እንዲመደብ እና ተጫዋቾች እንዲፈርሙ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሲመካከር ሰንበትበት ብሏል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ክለቡ አዲስ ቦርድ ያቋቋመ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ በአሰልጣኝነት የመሩት እስማኤል አቡበከር በክለቡ ይቀጥሉ ወይንስ አይቀጥሉ የሚሉ ተያያዥ ጉዳዮችን ለመወሰን የፊታችን ቅዳሜ አዲሱ ቦርድ ለውሳኔ ይቀመጣል፡፡ ለቀጣይ ዓመት በጀት እንደሚመደብ የሚጠበቀው ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ ጊዜ ያሳለፉትን ተጫዋቾች ውል ለማራዘም ቀጠሮ የያዙ ሲሆን ምንአልባት ተጫዋቾቹ በክለቡ ጥሩ ጥቅማጥቅሞችን ካገኙ ይቆያሉ ወይንስ ወደ ሌላ የሀገሪቱ ክለቦች ያመራሉ የሚለው ጉዳይ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ በክለቡ ግን ተጫዋቾቹ ላለመቀጠል የሚስማሙ ከሆነ ፊቱን ወደ አዳዲስ ተጫዋቾች ለማዞር እንደሚገደድ ይጠበቃል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ በቀጣይ ከአሰልጣኙ ጋር ይቀጥላል ? ወይንስ አይቀጥልም ? የሚሉትን ጉዳዮች እየተከታተልን ወደናንተ የምናደርስ ይሆናል፡፡