በከፍተኛ ሊጉ የደመቀው አማካይ ለሰበታ ከተማ ለመጫወት ተስማምቷል

የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት አዲስ አበባ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲገባ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች መሐል አንዱ የሆነው አማካይ ሰበታ ከተማን ለመቀላቀል ተስማምቷል፡፡

ብዙዓየው ሰይፉ ሰበታን ለመቀላቀል የተስማማው ተጫዋች ሆኗል፡፡ የትውልድ አካባቢው ባሌ ሮቤ ከተማን በአንደኛ ሊጉ ለሦስት አመታት በማገልገል የክለብ ህይወቱን የጀመረው ይህ አማካይ በመቀጠል 2011 ላይ በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሀላባ ከተማ አቅንቶ ሁለት የውድድር አመቱን በክለቡ በመጫወት ቆይታውን አድርጓል፡፡

በተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት አዲስ አበባ ከተማን መስከረም ወር መጨረሻ ላይ በመቀላቀል ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያልፍ ትልቁን ድርሻ ካበረከቱ ተጫዋቾች መሐል አንዱ መሆን የቻለው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ለቀጣዮቹ ሦስት የውድድር ዓመታት በሰበታ ከተማ መለያ ለመታየት ተስማምቷል፡፡

ያጋሩ