የዋልያው ሦስት ወሳኝ ተጫዋቾች ቀለል ያለ ጉዳት ገጥሟቸዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊት፣ የመሐል እና የኋላ መስመር ሦስት ተጫዋቾች ቀለል ያለ ጉዳት ማስተናገዳቸው ተሰምቷል።

ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ካለንበት ወር መጨረሻ ጀምሮ እንደሚያደርግ ይታወቃል። ለምድቡ ሁለት የመክፈቻ ጨዋታዎች ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ እያደረገ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑም በአሠልጣኙ እንደወጣው የዝግጅት መርሐ-ግብር በቀን አንድ እና ሁለት ጊዜ ልምምዱን እያከናወነ ይገኛል። በትናንትናው ዕለትም ልምምዱን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሰራው ቡድኑ ያለ ወሳኝ ተጫዋቾቹ ወደ ሜዳ እንደወጣ ሶከር ኢትዮጰያ አረጋግጣለች።

በትናንትናው ዕለት ከስብስቡ ጋር መደበኛ ልምምድ ያልሰሩት አቡበከር ናስር፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና አስቻለው ታመነ ናቸው። በዚህ ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት በነበረ ልምምድ ከተጫዋች ጋር በእንቅስቃሴ ተጋጭቶ መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደው ሱራፌል ትናንት ብቻ ሳይሆን ከትናንት በስትያም እረፍት ተሰጥቶት ልምምድ እንዳልሰራ ለማወቅ ችለናል። ይህ ቢሆንም ግን ተጫዋቹ ከደረሰበት መጠነኛ ጉዳት በጥሩ ሁኔታ እያገገመ እንደሆነ አረጋግጠናል።

ሁለተኛው ጉዳት ላይ የሚገኘው ተጫዋች ደግሞ አስቻለው ታመነ ነው። ትንሽ ጉዳት እያለበት ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀለው አስቻለው ምንም እንኳን አሁን ላይ ያለበት ጉዳት የሚያሰጋ ባይሆንም በጂም እና በሜዳ ላይ የአካል ብቃት ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ እና የተሻለ ለውጥ እያሳየ መሆኑን ተረድተናል።

እንደ አስቻለው መጠነኛ ጉዳት ኖሮት ስብስቡን የተቀላቀለው አቡበከር ናስርም ከቡድን አጋሮቹ ጋር ወጥቶ ሜዳ ላይ መደበኛ ልምምድ እየሰራ እንዳልሆነ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ምንም እንኳን ተጫዋቹ ጠንከር ያለ ጉዳት ላይ ባይገኝም እንደ አስቻለው እና ሱራፌል በኤክስኪዮቲቭ ሆቴል ቀለል ያሉ የጂም ልምምዶችን እያከናወነ የሦስት ቀን እረፍት እንደተሰጠው ሰምተናል።

እንደገለፅነው የሦስቱ ተጫዋቾች ጉዳት አስጊ የሚባል ባለመሆኑ ምናልባት አስቻለው እና ሱራፌል በቅርቡ ወደ ልምምድ እንደሚመለሱ ተመላክቷል። አቡበከር ግን ተጨማሪ እረፍት እንደሚሰጠውም ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ያጋሩ