ንግድ ባንክ የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ የምድብ ተጋጣሚዎቹን አውቋል

ከደቂቃዎች በፊት በድጋሚ በወጣው የሴካፋ የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር ድልድል ንግድ ባንክ ተጋጣሚዎቹን ለይቷል።

በቀጣይ ዓመት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የአፍሪካ ሀገራት የሊግ አሸናፊዎች በየዞናቸው የማጣሪያ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ይታወቃል። የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ክለብ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በሴካፋ ዞን ለሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ቢሾፍቱ ላይ መቀመጫውን በማድረግ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በተሳታፊ ሀገር ክለብ (የሩዋንዳው ስካንዲኒቪያን) ከውድድር መውጣት እንዲሁም በአስተናጋጅ ሀገር (ኬንያ) ዝግጁነት ምክንያት ሦስት ጊዜ የተራዘመው ይህ ውድድር ነሐሴ 22 መከናወን እንደሚጀምር የመጨረሻ ቀን እንደተቆራተለት መገለፁ ይታወሳል። በቅድሚያ የወጣው የምድብ ድልድልም በዘጠኝ ክለቦች መካከል መሆኑ ሲታወስ የሩዋንዳው ስካንዲኒቪያ ክለብ ራሱን ማግለሉን ተከትሎ ምድቦቹ ላይ መጓደል አምጥቷል። ይህንን ለማስተካከል ካፍ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ሴካፋ ከደቂቃዎች በፊት ማሟያ የተደረገበት ድልድል አውጥቷል።

ከሩዋንዳው ስካንዲኒቪያ ክለብ ጋር በቅድሚያ በምድብ ሦስት ተደልድለው የነበሩት የጂቡቲው ኤፍ ኤ ዲ ክለብ እና የኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ የምድብ አንድ እና ሁለት ክለቦችን አራት ለማድረግ እና የውድድሩን አጠቃላይ ምድብ ሁለት ለማድረግ እጣ ወጥቶላቸዋል። በዚህም በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኝበት ምድብ ሁለት የደቡብ ሱዳኑ ዪ ጆይንት ስታርስ እና የዛንዚባሩን ኒው ጄኔሬሽንን የውድድሩ አስተናጋጅ ሀገር (ኬንያ) ክለብ የሆነው ቪሂጋ ኩዊንስ እንዲገባ እጣ ወጥቷል።

በምድብ አንድ ደግሞ የጂቡቲው ኤፍ ኤ ዲ ክለብ የቡሩንዲው ፒ ቪ ፒ ፣ የዩጋንዳው ሌዲ ዶቭስ እና የታንዛኒያው ሲምባ ኩዊንስ ተቀላቅሏል።

በምድብ ሁለት የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያ ጨዋታውን ነሐሴ 23 ከኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

ያጋሩ