ከመስከረም 15 ጀምሮ በሚካሄደው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ውድድር ላይ ተካፋይ የሚሆኑ ስድስት ክለቦች በውድድሩ የስያሜ ባለቤት የተሰራላቸውን ልዩ መለያ በነገው ዕለት ይረከባሉ።
በስድስት ክለቦች መካከል ከመስከረም 15 ጀምሮ የሚደረገው የሲዳማ ዋንጫ ውድድር ሀገር በቀሉን የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ’ን የስያሜ አጋራ በማድረግ በሀዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ይታወቃል። የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ በሚል የሚካሄደው ውድድር የፊታችን ቅዳሜ በሀዋሳ ከተማ የሚጀመር ሲሆን ተሳታፊ ክለቦችም በውድድሩ የሚጠቀሙት መለያ በጎፈሬ ተመርቶ ማለቁን የተቋሙ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን ገልፀዋል።
ከሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የአጋርነት ስምምነት ባሳለፍነው ቅዳሜ የፈፀመው ጎፈሬ በውድድሩ ክለቦች የሚጠቀሙትን መለያ አቀርባለው ባለው መሠረት በሦስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ለእያንዳንዱ ክለብ የሚበረከቱ 35 የተጫዋቾች መለያዎች፣ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ቲሸርቶች፣ የአምበሎች የእጅ ጨርቆች እና ባንዲራዎችን አምርቶ መጨረሱን እና በነገው ዕለት ለክለቦች እንደሚያስረክብ ጠቁሟል።
አቶ ሳሙኤል ተቋማቸው በፍጥነት ጥራት ያለው ምርት ማዘጋጀቱን ለውድድሩ የሚዲያ አጋር ለሆነው ሶከር ኢትዮጵያ ገልፀው የየክለቦቹን የአካባቢ ባህል ለማስተዋወቅ በመለያዎቹ ላይ ታሪካዊ ይዘቶች እንዲኖር መደረጉን አውስተዋል።
“በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ባስታወቅነው መሠረት ጎፈሬ ከሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስምምነት የፈፀመው ባሳለፍነው ቅዳሜ ነው። በስምምነታችን መሠረት ለክለቦች የመወዳደሪያ ትጥቅ ለማቅረብ የተጣበበ ጊዜ ቢኖረንም ጥራቱን የጠበቀ ምርት ባለን ጊዜ አምርተን ጨርሰናል። ለክለቦቹም በነገው ዕለት ትጥቆቹን የምናቀርብ ይሆናል። ለስድስቱም ክለቦች የሰራናቸው መለያዎች ባህላዊ ይዘት እንዲኖራቸው አድርገናል። ማለትም የክለቦቹን አካባቢያዊ ትውፊት እና ታሪክ በቻልነው መጠን ለማስገባት ጥረናል። ለምሳሌ የሲዳማ ቡና መለያ ላይ ባህላዊ ጥለት እና ክለቡ ያለበትን አካባቢ የሚወክል ቡና እንዲሁም ጅማ አባጅፋር ላይም በተመሳሳይ የአካባቢው መገለጫ የሆነው ቡና እንዲታይ አድርገናል። በተጨማሪማ ሀዋሳ በደንብ የሚታወቅበት ሀይቅ፣ ሰበታ መለያው የሆነው አረንጓዴ ልምላሜ፣ ድሬዳዋ ታሪካዊው የባቡር ሀዲድ እና የዋሻ ውስጥ ምስሎች እንዲሁም የሀዲያ ሆሳዕና ባህላዊ ጥለት በክለቡ መለያ ላይ በጉልህ እንዲታይ አድርገን ምርቱን ጨርሰናል።” ብለውናል።
ከስር የተያያዙት መለያዎችም በነገው ዕለት በሀዋሳ በተዘጋጀ መርሐ-ግብር ለየክለቦቹ እንደሚበረከት ተመላክቷል።