የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዱራሜ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የ2013 የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በሀዋሳ ከተማ ሲደረግ ቆይቶ ዱራሜ ከተማን አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል።

(በብሩክ ሀንቻቻ)

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከሐምሌ 18 ጀምሮ በአርባ ስድስት ክለቦች በ11 ምድብ ተከፍሎ ሲደረግ የቆየው ወደ አንደኛ ሊግ የሚያልፉ ክለቦችን ለመለየት የተደረገው የ2013 የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ዛሬ ረፋድ በተደረጉ የደረጃ እና የፍፃሜ መርሀግብሮች ተቋጭተዋል፡፡

አቶ ኢሳይያስ ጂራ (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት)፣ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ (የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ)፣ አቶ ፍሬው አሬራ (የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር)፣ አቶ ብሩክ ቡናሮ (የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር)፣ አቶ ባህሩ ጥላሁን (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ዋና ፀሀፊ)፣ ቴዎድሮስ ፍራንኮ (የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዳይሬክተር እና የክለብ ላይሰንሲንግ ማናጀር) ፣ አቶ ከበደ ወርቁ (የፌዴሬሽኑ የውድድር ዳይሬክተር) እንዲሁም አቶ አንበሴ አበበ (የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ፕሬዝዳንት) በክብር እንግድነት በመዝጊያው ሥነ ስርአት ላይ በመገኘት ሁለቱም ጨዋታዎችን አስጀምረዋል፡፡

3:00 ሲል ሦስተኛ ደረጃ ለማግኘት የጋምቤላዉ ዐቢይ አካዳሚ እና የኦሮሚያ ክልሉ ቡሳ ከተማ ተገናኝተዉ በመደበኛዉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ጎል በመጠናቀቁ በተሰጠዉ የመለያ ምት የጋምቤላዉ አብይ አካዳሚ 5-4 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ዉድድሩን በሶስተኝነት በማጠናቀቅ የነሀስ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል።

በማስከተል ከ5:00 ጀምሮ የፍፃሜው ጨዋታ በምስራቅ ክፍለ ከተማ እና በዱራሜ ከተማ መሀል የተደረገ ሲሆን ዱራሜ ከተማ ተስፋፅዮን ዘለቀ እና መሪሁን መንቴ ሁለት ጎሎች የመጀመሪያውን አጋማሽ በመሪነት አጠናቀው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡ከእረፍት መልስ የሲዳማ ክልሉ ምስራቅ ክፍለከተማ በተሻለ የጨዋታ አቀራረብ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ ዱራሜ ከተማ የግብ ክልል በማምራት ከመመራት ተነስተው ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር አቻ መሆን ችለዋል። የዱራሜ ተከላካዮች በሳጥን ውስጥ የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ የሰጡትን የፍፃም ቅጣት ምት የምስራቅ ክፍለ ከተማዉ ግብ ጠባቂ ተስፋሚካኤል መቅድም ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል፡፡

በይበልጥ የመነቃቃት ስሜት ይታይባቸው የነበሩት ምስራቅ ክፍለ ከተማዎች መደበኛዉ የጨዋታ ክፍለ ደቂቃዎች ሊጠናቀቁ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ዳንኤል ደበበ ከሳጥን ውጪ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መለያ ምት ያመሩ ሲሆን 5-4 በሆነ ዉጤት የደቡብ ክልሉ ክለብ ዱራሜ ከተማ አሸንፎ የ2013 ሻምፒዮን ሆኗል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዕለቱ የክብር እንግዶች የተለያዩ ሽልማቶችን አበርክተዋል፡፡ በውድድሩ ላይ ለደመቁ ኮከቦች ሽልማት የማበርከት መርሀግብር ተካሂዷል፡፡ በኮከብ አሰልጣኝነት ወንድማገኝ ተሰማ ከዱራሜ ከተማ ፣ በኮከብ ተጫዋችነት ሄኖክ ሻውል ከምስራቅ ክፍለከተማ ፣ ሲሸለም በኮከብ ግብ ግብ ጠባቂነት መብራቱ ይሳቅ ከዱራሜ ከተማ ፣ በከፍተኛ ግል አግቢነት በአንፃሩ የምኅረት ክለቡ ቴዎድሮስ ተሸልሟል።

ውድድሩን ለመሩ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች ሽልማት የተበረከተ ሲሆን በልዩ ተሸላሚነት ደግሞ ሲመራ በነበረው ጨዋታ ላይ የቦዲቲ ተጫዋች በቡሳ ከተማ ተጫዋች ተመቶ ወድቆ ምላሱ የመተንፈሻ አካሉን በመዝጋት ላይ እያለ በፍጥነት ወደ ተጫዋቹ በማምራት ጣቶቹን አፉ ዉስጥ በመክተት የተጫዋቹን ህይወት የታደገው ፌዴራል ዋና ዳኛ ሀይማኖት አዳነ ልዩ ተሸላሚ ተብሎ ተሸልሟል። በዚህ ውድድር ላይ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ላደረጉ እና አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም የምስጋና ሰርተፊኬት እና የዋንጫ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ዉድድሩን በሶስተኝነት ላጠናቀቀዉ የዐቢይ አካዳሚ የነሀስ ሜዳልያ ሲሸለም ዉድድሩን በሁለተኝነት ያጠናቀቀዉ ምስራቅ ክፍለ ከተማ የብር ሜዳልያ፣ አሸናፊዉ ዱራሜ ከተማ ደግሞ የወርቅ ሜዳልያ ተሸልሟል።

የውድድሩ አዘጋጅ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን የዋንጫ ተሸላሚ የሆነ ሲሆን የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ም/ል ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ የተዘጋጀዉን ዋንጫ ተቀብለዋል። በስተመጨረሻም የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ተሸላሚ በመሆን በደቡብ ክልል ክለቦች ዋንጫ ተመሳሳይ የፀባይ ዋንጫን አግኝቶ የነበረው ዱራሜ ከተማ የተዘጋጀውን ዋንጫ ተቀብሏል።

ለማስታወስ ያህል ወደ ወደ 2014 አንደኛ ሊግ ያደጉ ክለቦች :-

ዱራሜ ከተማ፣ ምስራቅ ክፍለ ከተማ፣ ጋምቤላ ዐቢይ አካዳሚ፣ ቡሳ ከተማ፣ ዱከም ከተማ፣ ካማሺ ከተማ፣ ቦሌ ክፍለከተማ፣ ቫርኔሮ ወረዳ 13፣ ሊሙ ገነት፣ አዲስ ቅዳም ከተማ፣ ቦዲቲ ከተማ እና ኑዌር ዞን