የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት አካል የሆኑ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነሐሴ 28 ከጋና (ከሜዳው ውጪ) እንዲሁም ጳጉሜ 2 ከዚምባብዌ (በሜዳው) በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጉዞውን የሚጀምር ሲሆን ለእነዚህ የማጣርያ ጨዋታዎችም በአዳማ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። በቀጣይ ሳምንት ደግሞ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን እንደሚያከናውኑ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት የመጀመርዬው ጨዋታ ከሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ጋር ሲሆን ሐሙስ ነሐሴ 20 ጨዋታው ይደረጋል። ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ከዩጋንዳ ብሔራዊ ጋር ሲሆን ከሦስት ቀናት በኋላ እሁድ ነሐሴ 23 እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ፌዴሬሽኑ ስለ ወዳጅነት ጨዋታዎቹ ቀን ከመግለፅ ባለፈ የት እንደሚካሄድ ያልገለፀ ሲሆን ባደረግነው ማጣራት ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የሚካሄድበት ቦታ እንዳልተወሰነ እና ወደፊት እንደሚገለፅ ለማወቅ ችለናል።