የወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች ፍላጎት ምንድነው?

በክረምቱ መነጋገርያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊው ወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች በክለቡ ላይ ያነሱት ተቃውሞ እና ጥያቄ ይጠቀሳል። ይህ ጉዳይ ምንድነው ስንል ጠይቀን ተከታዩን ፅሁፍ አሰናድተናል።

በ2012 ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጉት ሠራተኞቹ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ሙሉ የውድድር ዘመናቸው መልካም አጀማመር ቢያደርጉም በተለይ ሁለተኛው የውድድር አጋማሽ ያጋጠመውን የውጤት መጥፋት ተከትሎ ቡድኑ በተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲናጥ መክረሙ እና በመጨረሻም በመለያ ጨዋታ የሊጉ ቆይታውን ማረጋገጡ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

የሜዳ ላይ የክለቦች ውጤታማነት አጠቃላይ በቡድኑ ዙርያ ያሉ ሁነቶችን በመወሰን ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይወጣል። በዚህም ክለቡ ውጤታማ በነበረባቸው ወቅቶች በብዙሀኑ ዘንድ እንደ ተግዳሮት የሚታዩ ጉዳዮች ለክለቡ በቀናዒነት በማሰብ ሲታለፉ የቆዩ ቢመስልም የቡድኑ ውጤት መንሸራተት ማሳየት ሲጀምር ጥያቄዎች መነሳት መጀመራቸውን ስናስተውል ቆይተናል። ታድያ አሁን ላይ እነዚህ ጉዳዮች ገፍተው ክለቡን አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገኝ አስገድደውታል።

በመሰረታዊነት በሀገራችን የክለቦች አወቃቀር ውስጥ የክለቦች ዋንኛው አካል የሆነው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ትልቁን ቦታ ይይዛል። በጠቅላላ ጉባዔውም የክለቡ ዓመታዊ ሪፖርት፣ የቀጣይ ዓመት ዕቅዶች ቀርበው ተገምግመው የሚፀድቁበት ፣ የክለቡ አጠቃላይ የፋይናንስ እና የኦዲት ሪፖርቶችን ጨምሮ ሌሎች በክለቡ አጠቃላይ ሂደት ላይ አይነተኛ ሚና ያላቸው አጀንዳዎች የሚነሱበት ዓመታዊ መድረክ እንደሌሎች ክለቦች ሁሉ በወልቂጤ ከተማ ስፖርት ክለብ ውስጥ ሲሰራበት የነበረ ቢሆንም ባለፉት ጊዜያት ግን ይህ መድረክ ሳይካሄድ ቀርቷል። ይህም መሆኑ ክለቡን በርካታ ጉዳዮች እንዳሳጣው ቢታመንም በተለይ ደግሞ የክለቡ አንድ አካል የሆኑት የክለቡ ደጋፊዎች በክለባቸው ዙርያ ቢሻሻሉ (ቢደረጉ) ብለው የሚያስቧቸውን ማናቸውንም ሀሳቦችን የማንሸራሸርያ መድረክ እንዲያጡ ያስገደደ ሆኗል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በተጠራው የደጋፊ ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ብዙሀኑ ደጋፊዎች በጉባኤው ላይ በሚቀርበው አጀንዳው አቀራረብ ዙርያ ላይ ከመግባባት ላይ ሳይደርሱ በመቅረታቸው ስብሰባውን አቋርጠው እስመውጣት ከዛም ባለፈ ወደሚመለከታቸው የበላይ አካላት ድረስ በመሄድ ለጥያቄዎቻቸው ተገቢ መልስ እንዲሰጣቸው ሲወተውቱ እንደነበረ በተለያዩ መንገዶች መታዘብ ተችሏል። ለመሆኑ የአብዛኛው የወልቂጤ ደጋፊዎች በመሠረታዊነት የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምድናቸው?

አንደኛው የደጋፊዎች ጥያቄ ክለቡ በጥቂት ሰዎች እየተዘወረ ይገኛል የሚለው ጉዳይ ነው። ክለቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምንም አይነት ኦዲት አድርጎ አለማወቁ ሌላኛው ተያያዥ ጥያቄ ነው። ሌላኛው ጉዳይ የክለቡ የቦርድ አባላት የስራ ዘመናቸው መጠናቀቁን ተከትሎ የአዳዲስ አመራሮች ምርጫ ይካሄድ የሚሉ እና ክለቡ ህዝባዊ መሠረት እንዲይዝ እና ግልፅ አሰራሮች እንዲሰፍኑ ይደረግ የሚሉ አንኳሮቹ ናቸው። ሆኖም እነዚህ ጥያቄዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በክለቡ ምላሽ ሳይሰጥባቸው መምጣታቸው ለአዲሱ የውድድር ዘመን የመዘጋጃ ጊዜ ከመቃረቡ ጋር ተደምሮ ሁኔታዎች የከረረ መልክ እንዳይዙ ስጋት ፈጥሯል።

ኢብራሂም ሰማን ይባላል። ከዚህ ቀደም የወልቂጤ የአዲስ አበባ ከተማ ደጋፊዎች አስተባባሪ ኮሚቴ ውክልና እንደነበረውና ሆኖም በክለቡ አመራሮች በኩል በሚደረጉ አንዳንድ ነገሮች ደስተኛ ባለመሆን ራሱን ከኃላፊነት በማግለል ክለቡ ትክክለኛ አቋም እንዲኖረው ሲታገል ሲባስተባብር እንደቆየ ይናገራል። ወልቂጤ ላይ በነበረው የደጋፊዎች ስብሰባ ወቅት ሰላማዊ ተቃውሞ ካሰሙ ደጋፊዎች መካከል አንዱ የነበረው ኢብራሂም ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ይህን ይላል።

” ወልቂጤ በነበረው ስብሰባ ከማንም ጋር ውይይት አላደረጉም። ብዙሀኑ ነው አቋርጦ የወጣው። ይህ የሆነው ደጋፊው ውይይት ከዚህ ቀደም ጠይቋል። አሁን ያለው ደጋፊ ማኅበር ከተመረጡ ሁለት ዓመት አልፎታል። በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ አንድም ቀን ከደጋፊ ጋር ስብሰባ አድርጎ አያውቅም። ይህ አካሄድ ተገቢ አይደለም። ክለቡ ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ አለበት በማለት እንቅስቃሴ ውስጥ ገባን። ባለፈው በነበረው ስብሰባ ወልቂጤ የሚኖረው ደጋፊም ሆነ እኛ ከአዲስ አበባ ተነስተን ስንሄድ የጠበቅነው ጠቅላላ ጉባዔ ይካሄዳል ብለን ነበር። ምክንያቱም ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅ ጠይቀን ምላሽ አልሰጡንም ነበር። አሁን የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ይሆናል ብለን አስበን ነበር። ሄድን ግን የጠበቀን ሌላ ነገር ነው። የክለቡን ክብር ባልጠበቀ ሁኔታ ባዶ አዳራሽ ወንበር የሌለው በዛ ላይ ያልተፀዳ ቆሻሻ የነበረ በቦታው ምንም አይነት የተሰቀለ የክለቡ አርማ የሌለበት አዳራሽ ሆኖ አገኘነው። በጣም ደነገጥን በግሌ አዘንኩኝ። ስብሰባ ነው ደጋፊው በዝቶ መጥቷል እንደዚህ ዓይነት ቦታ መግባታችን አሳዝኖናል። እንደዚህም ሆኖ ሁለት ትናንሽ ወንበር በመያዝ ካሚል የደጋፊ ማህበሩ እና እፀገነት የምትባል እንዲሁም የክለቡ ፕሬዝደንት መጥተው ቁጭ አሉ። አጠገባቸው አነስ ያለ ውይይት የሚል ፖስተር ሰቀሉ። ካሚል የስብሰባው አጀንዳ ውይይት እንደሆነ ተናግሮ አስኪጨርስ ጠበቅነው። ሲጨርስ እኛ ይህን ደጋፊ ማህበር አናቀውም የአመራር ዘመኑን ጨርሷል። ስድስት ወር አልፎታል። ስለዚህ እናንተ ልታወዩንም ልትሰበስቡንም አትችሉም። ከእኛም ምንም አይነት ጥያቄ ልትቀበሉን አትችሉም ብለን በሰላማዊ መንገድ ስብሰባውን አቋርጠን ወጣን። ከወጣን በኃላ ክለቡን በበላይነት የሚመራው ከንቲባው ቢሮ እና የከተማው ባህል ቢሮ ተቃውሟችን አሰማን። ማስተላለፍ የምንፈልጋቸውን መልዕክቶችን አስተላለፍን። ለሀገር ሽማግሌዎችም ምላሽ እንድናገኝ ደብዳቤ አስገብተን ተመለስን። ይህው እስካሁንም መልስ አልሰጡንም።

“የእኛ የመጀመርያ ጥያቄ ክለቡ ህዝባዊ እንዲሆን ነው። አሁን ክለቡ የህዝብ አይደለም። የሁለት እና የሦስት ሰዎች ነው። እንዳውም እነርሱ ክለባችን አይሉም ክለቤ ነው የሚሉት። ይህ መቀረፍ አለበት ክለቡ የህዝብ ነው። ሁለተኛ በክለቡ የሚሰሩ ማናቸውም ነገሮች ግልፅ እና ፍትሀዊ ታማኝነት እንዲኖር እንፈልጋለን። የሚሰሩ ስራዎችን በግልፅ አናቅም። ውስጥ ለውስጥ ነው የሚሰራው። ለደጋፊው ግልፅ እንዲደረግለት እንፈልጋለን። ሦስተኛ ክለቡ እውቀት ባላቸው እና ስፖርቱን በሚያውቁ ሰዎች እንዲመራ እንፈልጋለን። ቢያንስ ይዘውት የመጡት ነገር አለ እርሱን አመስግነን በክብር ሸኝተን የተሻለ አቅም ያላቸው ሰዎች ደጋፊው ማኅበረሰቡ ጋር ወርደው የሚሰሩ አመራሮች እንዲመጡ እንፈልጋለን። አራተኛ ክለቡ ኦዲት ተደርጎ አያቅም። እነርሱ ኦዲት ተደርጓል ይላሉ ግን የክለቡ ፅህፈት ቤት ገብታቹ ማየት ትችላላቹ ብትሄዱ ግን መረጃዎች የሚያሳያችሁ አካል የለም። ስንጠይቅም ደግሞ በየትኛውም መልኩ በግልፅ ለደጋፊው የሚናገር የለም። ከዚህ በተጨማሪ ተጫዋቾች ኮንትራት እያላቸው አብዛኛዎቹ መልቀቂያ እያስገቡ ነው። ምክንያቱ ምድነው ብለን ተጫዋቾቹን ስንጠይቃቸው አመራሮች የሚያደረጉን ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ንገሩን ስንላቸው ቃል እየተገባ የማይፈፀሙ ነገሮች በማለት ብዙ ነገር ይጠቅሳሉ። ሌሎች የሚያነሷቸውን ሀሳቦች ትቼ ማለት ነው። በአጠቃላይ እኛ እንደ ደጋፊ የክለቡ የዓመታት ችግር እንዲፈታ ጠቅላላ ጉባዔ መጠራት አለብን እንላለን።” ሲል ሀሳቡን ገልጿል።

ይህ በደጋፊዎች እና በክለቡ አመራሮች መካከል እየተካረረ የመጣው ልዩነት እስካሁን እልባት ሳያገኝ መቅረቱ ቡድኑ እስከ አሁን ድረስ በዝውውር መስኮቱ በንቃት እንዳይሳተፍ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ እንደሆነም ይታመናል። በመሆኑም በጉዳዩ ዙርያ የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት የእርምት እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ እና ይህ መጓተት የሚቀጥል ከሆነ ጅማሮ እየቀረበ በመጣው የሊጉ ውድድር ላይ ተካፋይ በሆነው ቡድኑ ውጤት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር የሚያሰጋ ጉዳይ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ የወቅቱ የክለቡ አመራሮችን ለማካተት በተደጋጋሚ ከፍተኛ ጥረት ብናደርግም ስልክ ባለማንሳታቸው ሊሳካልን አልቻለም።