ሀድያ ሆሳዕና የአማካዩን ውል አራዝሟል

ሆሳዕና የተከላካይ አማካይ ሥፍራ ተጫዋቹን ውል ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት አድሷል፡፡

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን ከቀጠረ በኋላ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ያካካተው እና የነባር ተጫዋቾችን ውልም እያራዘመ የከረመው ሀድያ ሆሳዕና ከነገ ነሐሴ 17 ጀምሮ የ2014 የቅደመ ውድድር ዝግጅቱን በሆሳዕና ከተማ ይጀምራል፡፡ለዚህም ለተጫዋቾቹ ጥሪ ያደረገው ክለቡ የተከላካይ አማካዩ ተስፋዬ አለባቸውን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመት በክለቡ እንዲቆይ ተስማምቷል፡፡

የቀድሞው የሰበታ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወልድያ እና ወላይታ ድቻ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ተስፋዬ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በሀድያ ሆሳዕና መለያ ያሳለፈ ቢሆንም ከክለቡ ጋር በተፈጠረ ያለመግባባት በመጨረሻዎቹ የሊግ ሳምንታት ክለቡን ማገልገል ካልቻሉ ተጫዋቾች መካከል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በክለቡ ውስጥ እንዲቀጥል ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ተጫዋቹ በክለቡ ለተጨማሪ ዓመት መቆየቱ እርግጥ ሆኗል፡፡