በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምሩት መቼ እንደሆነ ታውቋል።
በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አዳማ ከተማ የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ አለመሳተፋቸውን ተከትሎ በተከናወነ የማሟያ ውድድር በሊጉ መቆየቱን ማረጋገጡ ይታወሳል። ክለቡ በቀጣዩ ዓመት የሊጉ ውድድር ተጠናክሮ ለመቅረብም አዲስ አሠልጣኝ ከመሾም ጀምሮ በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ሲቀላቅል የከረመ ሲሆን አሁን ደግሞ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቼ እንደሚጀምር ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቋል።
በዚህም ክለቡ መቀመጫውን ባደረገበር አዳማ ከተማ የፊታችን ሰኞ ነሐሴ 17 ለመሰባሰብ ቀጠሮ መያዙ ተረጋግጧል። ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ሰኞ ከተሰባሰቡ በኋላም የህክምና ምርመራ እንደሚደረግ ታውቋል። ከዛ ክለቡ ረቡዕ ነሐሴ 19 በይፋ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚጀምር ተጠቁሟል።