በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ዛሬ በሁለት ጨዋታ ሲጀምር አዳማ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ አሸንፈዋል።
ለመጀመርያ ጊዜ በአራት ምድብ ተከፍሎ በአስራ ስድስት ቡድኖች መካከል ከነሐሴ 16 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን በባቱ ከተማ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የፕሪሚየር ሊግ እና የክልል ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
ጠዋት ሦስት ሰዓት በተካሄደው አዳማ ከተማን ከጋምቤላ ያገናኘው የምድብ ሀ የመክፈቻ ጨዋታ አዳማ ከተማ ብልጫ በመውሰድ 4-1 አሸናፊ ሆኗል። ሁለት የተለያየ መልክ ያለው የጨዋታ አቀራረብ ይዘው የገቡት ቡድኖቹ በአዳማ በኩል ኳሱን በተገቢ ሁኔታ በማደራጀት ክፍተት በመፈለግ የጎል እድሎችን መፍጠርን ሲያስመለክቱን በአንፃሩ ጋምቤላዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ተክለ ሰውነታቸውን ጉልበታቸውን እና ፍጥነታቸውን በመጠቀም አደጋ ሲፈጥሩ ተመልክተናል።
በአዲስ አበባ ውድድር ኮከብ ተጫዋች በመባል የተመረጠው ዮሴፍ ታረቀኝን መሠረት ያደረገው የቡድኑ አጨዋወት እንደወሰዱት ብልጫ በርካታ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በዋናነት የመስመር አጥቂው ሰይፈዲን እና ዮሴፍ ታረቀኝ ያልተጠቀሙባቸው እድሎች ጨዋታውን በጊዜ ለመቆጣጠር ያደረጉትን ጥረት አዘግይቶታል። ያም ቢሆን አዳማዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቀዳሚ መሆን ችለዋል።
በመልሶ ማጥቃት በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ የአዳማን የግብ ክልል አልፎ አልፎ የሚረብሹት ጋምቤላዎች ከመሐል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ በሚገባ ከተቆጣጠረ በኃላ ወደ ፊት በመግፋት ዊቺንግ ጆክ ወደ ጎልነት በቀየረው ኳስ ሆነዋል።
ጨዋታው በአዳማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቀጥሎ ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ከመስመር እየተነሳ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያስመለክተን ያረፈደው ሰይፈዲን ረሺድ ለአዳማ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጋምቤላዎች ጎል ቢቆጠርባቸውም የመጫወት ፍላጎታቸው ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ጨዋታው ከዕረፍት እንደተመለሰ ግን ሰይፋዲን ረሺድ አፈትልኮ ወደ ፊት በመሄድ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ የጋምቤላ እንቅስቃሴ አቀዝቅዞታል።
ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ተቀይሮ የገባው አስተርዕዮ አሸናፊ በግራ እግሩ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጋምቤላ በኩል አጥቂው ዊቺንግ ጃክ እና አማካይ ላኑኚር ከኚኩር ወደፊት ተስፋ የሚጣልባቸው ተጫዋቾች ሆነው አግኝተናቸዋል። በመጨረሻም የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ያረፈደው ሰይፈዲን ረሺድ ከቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አምበል ሳምሶን ሙሉጌታ እጅ ዋንጫ ተቀብሏል።
በመቀጠል የተካሄደው ሁለተኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማን ከኦሮምያ ክልል አገናኝቶ አዲስ አበባዎች በሙሉ ብለጫ 4-0 አሸናፊ ሆነዋል።
ከመጀመርያው ጨዋታ አንፃር ምንም እንኳን ጎል ይቆጠርበት እንጂ ቀዝቀዝ ያለ የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ጨዋታ ነበር። ጥሩ የተሟላ ስብስብ ይዞ የቀረበው አዲስ አበባ የኦሮሚያ ተከላካዮች ኳሱን ለማራቅ ብለው በፈጠሩት መደራረብ እዛው የቀረውን ኳስ የመከላከያ አጥቂ የነበረው በሙሉቀን በቀለ ቀዳሚ ጎል መሪ ሆነዋል። እንደ ቡድን በቂ የሆነ የዝግጅት እንዳላደረጉ የሚያስታውቁት ኦሮሚያዎች በግል ጥሩ የሚንቀሳቀሱ ተጫዋቾች እንዳሏቸው ተመልክተናል።
ጠንከር ያሉ የጎል ዕድሎችን መፍጠር የቀጠሉት አዲስ አበባዎች ሄኖክ ኤርምያስ ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት የኦሮምያው ግብጠባቂ ዳዊት ብሩክ ካመከነበት አጋጣሚ ሌላ ነፃ ኳስ አግኝቶ በድጋሚ ግብጠባቂው አድኖበታል። ይህ ቢሆን የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የዲኤፍቲው ኮከብ ሄኖክ ኤርሚያስ ለአዲስ አበባ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።
ከዕረፍት መልስ ኦሮሚያዎች ተነቃቅተው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ባለበት ወቅት በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው የኦሮሚያው ግብጠባቂ ዳዊት ብሩክ ለማራቅ የመታው ኳስ ከፊት ለፊት ለቆመው የአዲስ አበባው አጥቂ ሙሉቀን በቀለ ደርሶት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ብዙም ሳይቆይ የኦሮሚያው አሰልጣኝ ግብጠባቂው ዳዊትን ሰህተት ሰርቷል በማለት ቀይረው ማስወጣታቸው አግርሞትን ጭሯል።
ዱሬሳ ታደለ እና ይስሐቅ ይታገሱ አልፎ አልፎ በግላቸው ከሚያደርጉት ጥረት ውጭ የጎል ዕድሎችን መፍጠር የተቸገሩት ኦሮምያዎች በተወሰደባቸው ብልጫ በስተመጨረሻም በአዲስ አባው አጥቂ ሙሉቀን በቀለ አራተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል። ሙሉቀን የውድድሩ የመጀመርያው ሐት ትሪክ የሰራ ተጫዋች ሆኗል። ጨዋታውም ብዙም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በአዲስ አበባ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በኦሮሚያ በኩል አጥቂዎቹ ዱሬሳ ታደለ እና ይስሐቅ ይታገሱ ጥሩ አቅም ያላቸው ተስፈኞች እንደሆኑ አስተውለናል።
በጨዋታውም ኮከብ በመባል የአዲስ አበባው ሄኖክ ኤርሚያስ ሲመረጥ በጨዋታው ላይ ሐት ትሪክ መስራት የቻለው ሙሉቀን በቀለ የኳስ ከዕለቱ የክብር እንግዶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ17 ዓመት በታች አሰልጣኝ እንድርያስ እና ከፌዴሬሽኑ ምክትል ፀሐፊ አቶ ሰለሞን እጅ ተቀብለዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በየጨዋታዎቹ ኮከብ ተጫዋቾችን ከመምረጡ ባሻገር ከአስራ ስድስት ከሀምሳ ሳጥን ውጭ ጎል ለሚያስቆጥሩ ተጫዋቾች ልዩ ሽልማት ለመሸለም ዋንጫ ማዘጋጀቱ በጥሩ ጎኑ የሚጠቀስ ነው።
አዲስ የሚወጣው የምድብ ድልድል እና የነገው ስድስት ጨዋታዎች መርሐግብር እንደደረሰን አመሻሽ ላይ ይዘን እንመለሳለን።