አርባምንጭ ከተማ ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

በ2014 ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው አርባምንጭ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የሚጀምርበት ቀን ታውቋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሦስት ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ የምድብ ሐ ሻምፒዮን በመሆን ዳግም መመለሱን ያረጋገጠው አርባምንጭ ከተማ ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ቅድመ ዝግጅቱን የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ኮንትራት በማራዘም ቀጥሎም ደግሞ የአስር ነባር ተጫዋቾችን ውል ለተጨማሪ ዓመት እንዲራዘምላቸው በማድረግ እንዲሁም ሀቢብ ከማል፣ ሱራፌል ዳንኤል፣ አሸናፊ ተገኝ እና እንዳልካቸው መስፍንን በአዲስ መልክ በመቀላቀል ራሱን ለማጠናከር ሞክሯል፡፡

በዛሬው ዕለት ነሐሴ 17 ለተጫዋቾቹ ጥሪ ተደርጎ ሁሉም ተጫዋቾች ወደ ካምፕ የገቡ ሲሆን በነገው ዕለት የክለቡ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች የቅደመ ምርመራ እና የኮቪድ 19 ህክምናን በጣምራ ካከናወኑ በኋላ ረቡዕ ነሐሴ 19 በአርባምንጭ ከተማ ዝግጅቱን እንደሚጀምር አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በሴካፋ ውድድር ላይ አሰልጣኙ በባህር ዳር ተገኝተው የተመለከቷቸውን ሦስት የውጪ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ለማስፈረም በሒደት ላይ እንዳሉ የሰማን ሲሆን ክለቡም ከዲላ ከተማ አስፈርሞት የነበረውን አማካይ ፋሲል አበባየው ለወልቂጤ ከተማ መፈረሙ ይታወሳል፡፡