አዲስ አሠልጣኝ በመቅጣር በዝውውር ገበያው ላይ በንቃት የተሳተፈው ጅማ አባጅፋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል።
የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ አለመሳተፋቸውን ተከትሎ በሊጉ ለከርሞ መሳተፉን በማሟያ ውድድር ያረጋገጠው ጅማ አባጅፋር አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን በመንበሩ ከሾመ በኋላ ፊቱን ወደ ተጫዋቾች ዝውውር አዙሮ ነበር። በዚህም የነባር ተጫዋቾችን ውል እያደሰ በተለይ አዳዲስ ተጫዋቾችን መቀላቀል ላይ የተጠመደው ክለቡም ለ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዝግጅት የሚጀምርበትን ቀን አስታውቋል።
በዚህም ወጣት እና አንጋፋ ተጫዋቾችን ቀላቅሎ የያዘው ክለቡ ነገ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመጀመር ቀጠሮ እንደያዘ ለማወቅ ችለናል። ተጫዋቾቹ ቢሾፍቱ ላይ ነገ ከተሰባሰቡ በኋላም የጤና ምርመራ አድርገው በአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመሩ ልምምዳቸውን ከቀጣይ ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት ጀምሮ እንደሚቀጥሉ ታውቋል።