በወልቂጤ ከተማ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ከክለቡ ሥራ አስኪያጅ ጋር የተደረገ ቆይታ

👉 “…ቅፅ እና ማኅተም ተሰጥቶት ያንን ላልተገባ አላማ ሲያውል ተደርሶበት ከኃላፊነት የተነሳ ግለሰብ ነው”

👉 “ለተጫዋቾች የሚጠጡበት ቦታ ተመቻችቶ አንድ ወር ሙሉ መጠጥ ቤት እየጠጡ እንዲያመሹ ሲደረግ ነበር”

👉 “ከ80% በላይ የምንፈልጋቸውን ተጫዋችን ይዘናል”

የወልቂጤ ከተማ ዙርያ እየተነሱ ባሉ ጉዳዮችን በማስመልከት ባስነበብነው ፅሁፍ ዙሪያ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ላይ ዘግይቶ እንቅስቃሴ የጀመረው ወልቂጤ ከተማ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ባስመዘገበው ውጤት መነሻነት እና ተያያዥ የአስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተለይም ከዚህ ቀደም የወልቂጤ የአዲስ አበባ ከተማ ደጋፊዎች አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ ሚና ከነበረው ከአቶ ኢብራሂም ሰማን በኩል የተነሱ ቅሬታዎችን ማስነበባችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ “የክለቡ አመራሮችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም የተባለው ነገር አግባብ አይደለም፤ ከእናንተ በኩል ከእኔ ጋር በጉዳዩ ዙርያ የተገናኘ አካል ባለመኖሩ በዚህ ቅር መሰኘታችንን እንገልፃለን።” ያሉን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ታዬን ሀሳቦች እንዲህ ልናስነብባችሁ ወደናል።

ስለክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ እና የጠቅላላ ጉባዔ ጉዳይ

በእኛ ግምገማ ክለባችን እንደሚባለው ችግር ውስጥ ነው የሚል እንድምታ የለንም። ክለቡ ምንም ዓይነት ችግር ውስጥ አይገኝም። እንደከዚህ ቀደሙ ሥራዎችን እየከወነ ይገኛል። ከደጋፊዎች ጋር በተገናኘ የሚነሱ ጥያቄዎችን ምክንያት በማድረግ ‘ክለቡ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል’ የሚለው ጉዳይ ተገቢ አይደለም። በአንድ ክለብ ውስጥ ደጋፊ እንደ ደጋፊ የራሱ ድርሻ አለው። ክለቡ ደግሞ ራሱን የቻለ ከመንግሥት ጋር ተገናኝቶ የሚሰራበት አወቃቀር አለው። የክለብ እና የደጋፊ ማኅበራት አወቃቀር የተለያየ መሆኑ ግልፅ ሊሆን ይገባል። ከ2012 ጀምሮ በኮቪድ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ከደጋፊ ማኅበሩ ጋር ውይይቶች ነበሩ። ይህም አሰራር የተዘረጋው በ2011 አዲስ የክለብ አመራር ተመርጦ ነው በዚህ መንገድ መሥራት የጀመርነው። በክለባችን አሰራርም የደጋፊ ማኅበር የራሱ የሆነ ጠቅላላ ጉባዔ አለው። ክለቡም ራሱን የቻለ ቦርድ ነው ያለው። ደጋፊው የሚያነሳው ጠቅላላ ጉባዔ ሊሆን የሚችለው ሊያነሳ የሚገባውም የማኅበሩን ራሱን እንጂ የክለቡን አይደለም። ትልቁ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይም የሁለቱ ልዩነት ነው። ጠቅላላ ጉባዔ መዋቅርን መሰረት ያደረገ ቅርፅ ነው የሚይዘው። ክለቡ ገና ሕዝባዊ መሰራት አለመያዙ መታወቅ አለበት ፤ እየተመራ የሚገኘው በመንግሥት ድጎማ ነው። ዞሮ ዞሮ ግን እንደዛም ሆኖ እኛ የደጋፊ ማህበር አዋቅረን ራሱን የቻለ ቅርፅ እንዲኖረው አድርገን ፣ ፅህፈት ቤት አደራጅተን አቋቁመናል። ሆኖም ማኅበሩ ክለቡን መደገፍ ሲገባው እኛ ነን እንደውም እንደ ክለብ ድጋፍ እያደረግንለት የምንገኘው።

በዋናነት ግን ማኅበሩ ከደጋፊዎች የተውጣጣ የራሱ ጠቅላላ ጉባዔ ሲኖረው ክለቡ ደግሞ የመንግሥት ተቋማትን ፣ የግል ድርጅቶችን ፣ ባለሀብቶችን መሰረት ያሰረገ የራሱ የሆነ ጠቅላላ ጉባዔ ነው የሚኖረው። እስካሁን ክለቡ ጠቅላላ ጉባዔ አልነበረውም። ህዝቡ የለመደው እና አሁን ቅሬታ ያነሳው አካል በተለምዶው በሞንታርቮው ህዝብ ተጠርቶ የሚደረገውን ስብስባ ነው እንደ ጠቅላላ ጉባዔ የለመደው። ነገር ግን አሰራሩን በተከተለ መንገድ ካልሆነ በግለሰብ ደረጃ ሪፖርት አይደረግም። እኛም እየተከተልን ያለነው ያንን ነው። የጠቅላላ ጉባዔ ምስረታ ይኖራል፤ ምስረታው ላይ ከላይ የተነሳውን አቅጣጫ ይዘን ነው የምንሄደው። ይህንን የመረዳት የግንዛቤ ችግር በመኖሩም ነው ትልቅ ችግር የሆነው እንጂ ክለቡ ውስጥ ብዙ ችግር ኖሮ አይደለም።

በቅርቡ ስለተደረገው ስብስባ

ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያው ስለክለቡ መልካምም አሉታዊም የሆኑ ነገሮች ይነሱ ስለነበር ያን መሰረት በማድረግ እና የተለያዩ ግለሰቦች ወደተለያዩ የዞን እና የከተማ አስተዳደሮች ጋር ስለሚሄዱ ‘የውይይት መድረክ ቢዘጋጅ ጥሩ ነው’ በሚል ከዞን እና ከተማ አስተዳደሮቹ ጋር ተነጋግረን ደጋፊ ማህበሩ ነፃ የውይይት እንዲያመቻች አቅጠጣጫ አስቀምጠናል። ያንን ነፃ የውይይት መድረክ ደጋፊ ማኅበሩ አዘጋጅቷል። መድረኩንም የመራው እንደ አደራጅ መሥሪያ ቤት የስፖርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ከደጋፊ ማኅበሩ ጋር በመሆን ነው። እኛ ደግሞ በቦታው በመገኘት የሚነሱ ጉዳዮችን ለመስማት እንደክለብ አመራር ተገኝተናል። ግን የተደራጀው ኃይል ጠብቀው የነበረው ቅድም እንደተናገርኩት ከህግ እና አሰራር ውጪ ከዚህ በፊት እንደሚደረገው በሞንታርቮው ተጠራርቶ ማድረግ ነው። ያንን አሠራር ደግሞ አስቀርተናል። ከዚህ በኋላ የምንጓዘው በህግ እና ስርዓት ስለሆነ። ትልቁ ክፍተት ያ ነው።

ከኦዲት ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች

ከኦዲት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ። ክለቡ የሚመራው በመንግሥት ድጎማ ነው። መንግሥት የዓመቱ በጀት ሲዘጋ በቦርድ የሚመራ ህጋዊ ኦዲተር ተልኮ ይታያል። አሁን ራሱ ኦዲተሮች ቢሯችን አሉ የዚህን ዓመት ለመመርመር። ባለፈውም ዓመት፣ በ2011 ከዛም በፊት በየዓመቱ ተደርጓል። ስለዚህ የዚህን ዓመት የኦዲት ሪፖርት ብቻ ነው እየጠበቅን ያለነው። እውነታው ይህ ነው። ከዛ ውጪ ግን ኦዲት ተደርጎ አያውቅም የሚባለው ነገር የተሳሳተ ነው። ያለፉት ዓመታት የኦዲት ሪፖርትም መመልከት ይቻላል። በመሠረቱ ህዝባዊ ቢሆን ኖሮ ግዴታ ሪፖርቱ ለጠቅላላ ጉባዔው መቅረብ አለበት። አሁን ግን መንግሥት ስለሚደጉመን በመንግሥት አሠራር መሠረት ወደድንም ጠላንም ኦዲት እንደረጋለን።

በቦርድ አመራሮች ላይ ስላለው ተቃውሞ

በደጋፊ ተቃውሞ አለ ተብሎ የሚነሳው የቦርድ አመራር አባላትን በተመለከተ ነው። ይህም ምላሽ የሚያገኘው በጠቅላላ ጉባዔ እንጂ ደጋፊው ወይም በደጋፊ ማኅበሩ አይደለም። የቦርድ አመራር በደጋፊ ምርጫ አይደለም የሚቀመጠው። እነሱ ሊቃወሙ የሚችሉት የደጋፊ ማኅበሩን ቦርድ ነው እንጂ የክለቡን አመራር የመሾምም ሆነ የማንሳት ሥልጣኑ ያለው ጉባዔው ነው። ይህ ደግሞ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ይያያዛል። በክለቡ መተዳደርያ ደንብ መሠረት የከተማው ከንቲባ የክለቡ የበላይ ጠባቂ ነው። የከተማው የስፖርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ደግሞ የክለቡ ፕሬዝዳንት ይሆናል። ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ፀሐፊ እና ሌሎች የቦርድ አባላት ደግሞ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተውጣጥቶ በከንቲባውና በስፖርት ፅሕፈት ቤት በኩል ፕሮፖዝ ተደርጎ ነው የሚመረጠው። ያ የሆነው የጠቅላላ ጉባዔ ምስረታ ስላልተደረገ ነው። አሁን ግን ያንን ጠቅላላ ጉባኤ ምስረታ ለማካሄድ የዘንድሮውን የኦዲት ሪፖርት እንጠብቃለን። በተጨማሪም የከተማ አስተዳደር ምክርቤት ጉባኤውን አካሂዶ በጀት የሚያዝበት መንገድ እስኪመቻች ነው። እንግዲህ ይህን አካሄድ ካለማወቅ ብቻ ሳይሆን እየታወቀም ለሌላ አላማ እና ተልዕኮ የሚኬድባቸው ነገሮች ስላሉ ነው። 

ክለቡ የሚተዳደረው በመንግሥት ድጎማ ነው። ከመንግሥት ጋር ተናበን እየሰራን ነው። ተቃውሞው ተገቢ አልነበረም። ከንቲባውን ጭምር እስከመሳደብ የደረሰ ነበር የባለፈው ሰልፍ። አዳራሽ ለቆ የወጣው ውስን አካልም ያራመደው የራሱን ሀሳብ ነበር።

በተጨዋቾች ዙሪያ ስለሚነሱ ጥያቄዎች

ከተጫዋች ጋር በተያያዘ በእርግጥ ክለቡ በዓመቱ መጨረሻ የውጤት ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ከፕሪምየር ሊጉም ወርዶ ነበር። በአጋጣሚ በትግራይ ክልል ክለቦች አለመሳተፍ ምክንያት ሌላ ዕድል አግኝተን ባንመለስ ኖሮ ወርዶ ነበር። እሱ ላይ ምንም የሚያጠያይቅ ነገር የለም። ስለዚህ እንዲወርድ ካደረጉ ነገሮች መካከል ያሁኑ ዓይነት ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች ውድድር ላይ በነበርንበት ወቅትም ነበር። ተጫዋቾች ላይ የሥነ ልቦና ችግር የሚፈጥሩ ፅሁፎች በተለያዩ የውሸት የፌስቡክ አካውንቶች ሲፃፉ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ በወልቂጤ ዙርያ የሚያተኩሩ የውሸት አካውንቶችን በብዛት የሚበልጥ ያለ አይመስለኝም። ያ በተጫዋቾች ሥነ ልቦና ላይ ከፍተኛ ጫና ሲፈጥር ነበር። ግለሰቦች በጀት መድበው ተጫዋቾችን ያልተገቡ ድርጊቶች ውስጥ እንዲገቡ ሲያደርጉ ነበር። ለምሳሌ ለተጫዋቾች የሚጠጡበት ቦታ ተመቻችቶ አንድ ወር ሙሉ መጠጥ ቤት እየጠጡ እንዲያመሹ ሲደረግ ነበር። በዚህም ክለቡ በመጨረሻ ጨዋታዎች በሊጉ ለመቆየት የነበረውን ዕድልም እንዳይጠቀም ሲደረግ ነበር። ያም አልፎ በማሟያ ውድድሩ ተወዳድሮ በሊጉ እንዲቀጥል ተደርጓል። በዚህ የዲሲፕሊን ችግር ውስጥ የነበሩ ወደ ሰባት ተጫዋቾች በደሞዝ እንዲቀጡ ወይም ኮንትራታቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል። ሌላው ውጤታማ ባለመሆናቸው ተጫዋቾች እና የ ቡድን አባላት ተነስተዋል። እነሱ ናቸው እንደ ደጋፊ ሆነው ይህን ነገር የሚያስተባብሩት። የደጋፊ ጥያቄ እንደሆነ ተደርጎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎችም የሚቀርበው በነዚህ አማካኝነት ነው።

ስለ አቶ ኢብራሂም ሰማን

ሌላው በሶከር ኢትዮጵያ ላይ በወጣው ፅሁፍ ላይ የተጠቀሰው ኢብራሂም ሰማን የተባለው የወልቂጤ ደጋፊ ነኝ የሚል ግለሰብ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ያሉ የከተማው ተወላጆችን ፣ ደጋፊዎች እና ክለቡ የሚወዱ አካላትን እንዲያስተባብር እና በደጋፊ ማኅበሩ በኩል የደጋፊነት መታወቂያ አውጥተው እንዲደጎፉ ለማድረግ ቅፅ እና ማኅተም ተሰጥቶት ያንን ላልተገባ አላማ ሲያውል ተደርሶበት ከኃላፊነት የተነሳ ግለሰብ ነው። እውነታው ይህ እንጂ በእናንተ ፅሁፍ ላይ እንደቀረበው በራሱ ፈቃድ ራሱን አግልሎ አይደለም። ኃላፊነት ሰጥቶት የነበረው የደጋፊ ማኅበሩ ነው። ያንን ኃላፊነት ባለመወጣቱ እና የራሱን ጥቅም ለማካበት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ አስቁመናል።

በዝውውር ጉዳዮች ላይ ስለሚነሱ ጥያቄዎች

ከዝውውር ጋር ተያይዞ አምና የነበረ ክፍተት ገምግመን ተጫዋቾችን እያስፈረምን እንገኛለን ፤ በእርግጥ ለሚዲያ ይፋ ያላደረግናቸው ቢኖሩም። በተጨማሪ ብዙ ተጫዋቾች አናስፈርምም። ምክንያቱም ባለፈው ዓመት በርካታ ተጫዋች በሁለት ዓመት ኮንትራት ስላስፈረምን ቡድን እያፈረስን አንገነባም። የለቀቁ ተጫዋቾችም ሊበዙ የቻሉት በዲሲፕሊን ግድፈት እና ውል ያጠናቀቁትን በተሻለ ተጫዋች ለመተካት በመወሰናችን ምክንያት ነው። ውል እያላቸው ብዙም ያላገለገሉንንም በስምምነት ለቀናል። በአጠቃላይ ከ80% በላይ የምንፈልገው ተጫዋችን ይዘናል። አሁንም ክፍተቶቻችንን ሊያሟላ በሚችል መልኩ እንቅስቃሴ ላይ ነው ያለነው። ለምሳሌ በአፍረካ ደረጃ ከፍ ያለ አቅም ያለው ግብ ጠባቂ ዝውውርን እያጠናቀቅን ነው። በተጨማሪም ለተጫዋቾች የምንከፍለው ከፍተኛ ክፍያ እስከ ስንት ድረስ ነው የሚለውን ከመንግሥት መልስ ማግኘት ስለነበረብን ለማዘዋወር መዘግየቶች ታይተውብን ነበር።

ከውጪ ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ ለመጠቀም ወስነን ነበር። ለሀገሪቱም እግርኳስ ጥቅም የሚኖረው ባለን ሀይል ብንጠቀም ነው ብለን ወስነን ነበር ያስቀረነው። ሆኖም አምና የነበረውን ሂደት ገምግመን የሀገራችን ተጫዋቾች ፕሮፌሽናሊዝም ላይ ጥያቄ እየተነሳ ስለሆነ ነው ይህን ሀሳብ ቀይረን የውጪ ተጫዋቾች ለማካተት የወሰንነው ።

ስለክለቡ ቀጣይ ዕቅዶች

መስራች ጉባዔው ሊጉ ከመጀመሩ በፊት እናደርጋለን ብለናል። እስከ መስከረም አጋማሽ ባለው ጊዜ የጠቅላላ ጉባዔ ምስረታ አከናውነን የመተዳደርያ ደንብ እና ሌሎች ነገሮችን እናፀድቃለን። ጠቅላላ ጉባዔው የመግስት አደረጃጀትን መሰረት ያደረገ ይሆናል። እስከ ቀበሌ ድረስ የሚወርድ የመንሥስት መዋቅር አለ፤ የስፖርት ማኅበራት ማቋቋምያ አዋጅም አለ። በዛ መሠረት የግል ባለሀብቶችን፣ የንግድ ማኅበራትን፣ አምራች ድርጅቶችን፣ የስፖርት ማኅበራትን፣ የደጋፊ ማኅበር፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን፣ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደሮችን ባማከለ መልኩ ነው የሚደራጀው።

ክለቡን በአክሲዮን ማኅበር አደራጅቶ ለመሸጥ ፕሮፖዝ ተደርጎ ተሰርቷል። ነገር ግን እንደ አጠቃላይ ክለቡ በመጀመርያ ከመንግሥት መውጣት አለበት። ይህን ካቢኔው ተወያይተበት አፅድቆታል። ነገር ግን ወደ መሬት ለማውረድ ረጅም ጊዜ ይፈጃል። ዕቅዱም የአንድ እና ሁለት ሳይሆን የረጅም ጊዜ ነው። መንግሥትም መዘጋጀት ስላለበት ጊዜ ይፈልጋል። በአጠቃላይ ግን ጥናት ተጠንቶ በባለሙያዎች እየተሰራ ነው ያለው። ክለቡ በራሱ የፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አባል ነው። ከመንግሥት አሰራር አንፃርም የአክሲዮን ማኀበር ውስጥ ሆነን መንግሥት ጋር መቀመጥ አንችልም። ስለዚህ ከመንግሥት ጋር ያለውን ነገር ጨርሰን የምንሄድበት ጉዳይ ነው የሚሆነው።