በ2022 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሩዋንዳ አቻውን የሚገጥመው የአሠልጣኝ ፍሬው ወልደገብርኤል ስብስብ ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ተገልጿል።
በ2022 በኮስታ ሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ሀገራት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ መጀመራቸው ይታወቃል። በአህጉራችን አፍሪካ የሚገኙ እና ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ሀገራትም የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ባሳለፍነው ሳምንት አከናውነው ያገባደዱ ሲሆን የሁለተኛ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ደግሞ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ መደረግ ይቀጥላሉ። በአሠልጣኝ ፍሬው ወልደገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም በሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የሩዋንዳ እና ደቡብ ሱዳን አሸናፊን ለመግጠም መርሐ-ግብር ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ደቡን ሱዳን ከውድድሩ ራሷን በማግለሏ የቀጣይ ዙር የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ሩዋንዳ መሆኗ ተረጋግጧል።
የመጀመሪያዋ የሩዋንዳ እንስት ፕሮፌሽናል አሠልጣኝ በሆነችው ናይናዋሙንቱ የሚመራው የሩዋንዳ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድንም ከሁለት ሳምንት በፊት ለ39 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅት መጀመሩን ዘግበን ነበር። አሁን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ያገኘነው መረጃ ደግሞ አሠልጣኝ ፍሬው ዛሬ አልያም ነገ ለተጫዋቾች ጥሪ እንደሚያቀርቡ ያመላክታል። በካፍ የልዕቀት ማዕቀል መቀመጫውን አድርጎ እንደሚዘጋጅ የሚጠበቀው ቡድኑም የፊታችን ሀሙስ (ነሐሴ 20) ልምምድ እንደሚጀምርም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከመስከረም 13-15 ሩዋንዳ ላይ ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከመስከረም 27-29 ኢትዮጵያ ላይ እንደሚደረግ የወጣው መርሐ-ግብር ያመላክታል።