ጦሩ ጋናዊ የግብ ዘብ አስፈርሟል

የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ቢሾፍቱ ላይ እያከናወነ የሚገኘው መከላከያ ከደቂቃዎች በፊት ግብ ጠባቂ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው መከላከያ አዳዲስ ተጫዋቾችን በመቀላቀል ለ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዝግጅቱን ቢሾፍቱ ላይ ማድረግ ከጀመረ ቀናቶች ተቆጥረዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ጋናዊውን የተከላካይ አማካይ ኢማኑኤል ላሪያን በአንድ ዓመት ውል አስፈርሞ የነበረው ክለቡም ዛሬ ሌላ ጋናዊ ተጫዋች የግሉ ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብቶ ለክለቡ ፊርማ ያኖረው ግብ ጠባቂ ክሌመንት ቦዬ ነው። ከዚህ ቀደም ለሀገሩ ክለቦች ኸርትስ ኦፍ ኦክ እና አሜደስ ኢንተርናሽናል እንዲሁም ለደቡብ አፍሪካው ቢድቬስት ዊትስ ተጫውቶ የነበረው ክሌመን ቦዬ ከስድስት ወራት በፊት ወደ ማልታው ክለብ ሳን ግዋን አምርቶ የነበረ ቢሆንም ከግማሽ ዓመት ቆይታ በኋላ ከቡድኑ ተለያይቶ ወደ መከላከያ አምርቷል። 2009 ላይ በደደቢት መለያ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ የደረሰው ተጫዋቹም የአንድ ዓመት ውል መፈረሙ ታውቋል። ለሁለት የውድድር ዘመናት በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹም በደደቢት አብረውት ከሰሩት አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ጋር በድጋሚ የሚገናኝበት ዕድል ተፈጥሯል።