ባሳለፍነው ሳምንት የወጣውን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድልን በተመለከተ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ገለፃ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች እያደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ዛሬ ከሰዓት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ መግለጫ ሰጥተዋል። ዝግጅታቸውን በተመለከተ የተነሳውን ሀሳብ ከደቂቃዎች በፊት ያስነበብን ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት የወጣውን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል በተመለከተ አሠልጣኙ የተናገሩትን ንግግር ደግሞ አሁን ይዘን መጥተናል።
በካሜሩን ርዕሰ መዲና ያውንዴ የካፍ የውድድር ዳይሬክተር ሳምሶን አዳሙ በቀድሞ ተጫዋቾቹ ዲዲየር ድሮግባ፣ ሳሙኤል ኢቶ፣ ራባህ ማጄር፣ ጋዬል ኢንጋናሙቲ እና አሳሙዋ ጂያንን እየመራ ባወጣው ድልድልም ዋልያው ከካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቨርዴ ጋር መደልደሉ ተረጋግጧል። ይህንን የምድብ ድልድል እንዴት ይመለከቱታል ተብለው የተጠየቁት አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ተከታዩን አጭር ሀሳብ ተናግረዋል።
“የአፍሪካ ዋንጫ ድልድልን በተመለከተ እኛ ቋት 4 ላይ ነበርን። ከበላያችን ያሉት ሦስት ቋቶች ውስጥ ደግሞ ጠንካራ ቡድኖች ናቸው ያሉት። በህጉ መሰረት ደግሞ እኛ በሌሎቹ ቋት ውስጥ ካሉ ጠንካራ ቡድኖች ጋር ነው የምንደለደለው። የሆነውም ይህ ነው። ከዚህኛው ጠንካራ ቡድን ይሄኛው ጠንካራ ቡድን ይሻላል የሚለው ሌላ ነገር ነው። ብቻ እኛ ቋት ውስጥ ከነበሩት ቡድኖች ጋር አይደርሰንም ነበር። ስለዚህ በደረጃ ከሚበልጡን ጋር ተመድበናል። ግን በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ነገር እንደ ትናንቱ በፍራቻ አይደለም የምንጫወተው። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ በርከት ያሉ ግቦችን እያገባን በጥሩ አጨዋወት ስንጫወት ነበር። ስለዚህ በቀጣይም ይህ ይቀጥላል። እስከ ጥር የተወሰነ ጊዜ ስላለን የጀመርነውን ነገር እያስቀጠልን እንሄዳለን። በአጠቃላይ በምድባችን የተለየ ነገር ለማሳየት እንሞክራለን።”