በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከናወነው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ከፊቱ የዞን የማጣሪያ ውድድር ያለበት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ይገኛል።
በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የአራት ጊዜ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የሊጉ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከናወነው የአህጉሩ የእንስት ክለቦች ውድድር ላይ የመሳተፍ ዕድሉን አግኝቷል። እርግጥ በቀጣይ ዓመት በግብፅ አስተናጋጅነት ስምንት ክለቦችን ብቻ በማሳተፍ የሚደረው ውድድር ላይ ክለቡ በቀጥታ መሳተፉን ባያረጋግጥም በሴካፋ ዞን በሚደረግ ውድድር ዋናውን ትኬት የሚቆርጥ ይሆናል። በዚህም ክለቡ በምድብ ሁለት ከደቡብ ሱዳኑ ዪ ጆይንት ስታርስ፣ ከዛንዚባሩን ኒው ጄኔሬሽንን እና ከኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ ጋር ተደልድሏል።
ታዲያ በቀጠናው ለሚደረገው የማጣሪያ ውድድር አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን በመቀላቀል ዝግጅቱን ቢሾፍቱ ላይ የጀመረው ክለቡም በጥሩ ሁኔታ ልምምዱን እየሰራ እንደሆነ ለመታዘብ ችለናል። እስከ ዛሬ ድረስ 42 የልምምድ ቀናትን ያሳለፈው ክለቡም በኬንያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው ውድድር ሁለት ጊዜ ሲራዘም ለተጫዋቾቹ እረፍት ሰጥቶ የነበረ ሲሆን የውድድሩ መከናወኛ ጊዜ ከተቆረጠ በኋላ ግን ባለፉት አስራ አንድ ቀናት የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቱን ሲከውን ነበር።
ሶከር ኢትዮጵያ ዛሬ ወደ ቢሾፍቱ አቅንታ በተመለከተችው የቡድኑ የልምምድ መርሐ-ግብር ላይም ሁሉም ተጫዋቾች (21) በመልካም ጤንነት ላይ በመገኘት ጠንከር ያለ ልምምድ ሲሰሩ ነበር። እስከ እሁድ ድረስ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ ሲሰራ የነበረው ስብስቡም ከትናንት ጀምሮ ጠዋት ላይ ብቻ ልምምድ መስራት ቀጥሏል። በዛሬው ዕለትም ቡድኑ 2:20 የቆየ ልምምድ ሰርቷል።
በዛሬው ልምምድ ላይ ተጫዋቾች በአሠልጣኝ ብርሃኑ እና ምክትሉ ኤርሚያስ እየተመሩ ኳስን መሠረት ያደረጉ ሥራዎችን ሲሰሩ አስተውለናል። በተለይ ዋና አሠልጣኙ የማጣቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ለብቻቸው ረዳቱ ደግሞ የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ነጥሎ ማጥቃት እና መከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና ሲሰጡ ነበር። ዘለግ ያለ ደቂቃ ከፈጀው ልምምድ በኋላም አጥቂዎቹ ግብ ባስቆጠሪያ ስልት የሚያገኙበትን ክፍተት ለማግኘት የሚያስችላቸው ልምምድ ሲሰሩ ነበር። በመጨረሻም አሠልጣኝ ብርሃኑ ቡድኑን ለሁለት ከፍለው በግማሽ ሜዳ የ30 ደቂቃ ግጥሚያ እንዲያከናውኑ አድርገዋል።
በቢሾፍቱ የነበረውን ዝግጅት በነገው ዕለት የሚያገባድደው ክለቡ ረፋድ ላይ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቶ ከሰዓት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ ለማወቅ ችለናል። ስብስቡም ነገ አዳሩን በመዲናው ካደረገ በኋላ ሀሙስ ቀን 5 ሰዓት ወደ ኬንያ የሚያመራ ይሆናል። የመጀመሪያ ጨዋታውንም ከውድድሩ አስተናጋጅ ሀገር ክለብ ቪሂጋ ኩዊንስ ጋር ነሐሴ 23 በንያዮ ስታዲየም የሚያከናውን ይሆናል።