አዳማ ከተማ አራት ወጣቶችን ከተስፋ ቡድን አሳድጓል።
በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እና በረዳቱ ይታገሱ እንዳለ መሪነት በዛሬው ዕለት ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረው አዳማ ከተማ የወሳኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር በክረምቱ የዝውውር መስኮት የፈፀመ ሲሆን ልምድ ያላቸውን ከወጣቶች ጋር በማቀናጀት በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ብቅ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዕድሜ እርከን ውድድሮች በተደጋጋሚ ውጤታማ የሆነው ክለቡ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት አራት ወጣት ተጫዋቾችን ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ማሳደጉን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡ዳዊት ይመር (ተከላካይ) ፣ በላይ ጌታቸው (ተከላካይ) ፣ አብዲ ዋበላ (አጥቂ) እና አቤል ደንቡ (አጥቂ) ወደ ዋናው ስብስብ ማደጋቸው የተረጋገጠ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም የክለቡ የቢ ቡድን ተጫዋች ለነበሩት ለጅብሪል አህመድ እና ለዘካሪያስ ፍቅሩ የሙከራ ዕድልንም ሰጥቷል፡፡
ክለቡ ከስድስት ወራት በፊት በተመሳሳይ ቢንያም አይተን (አጥቂ) ፣ ሙአዝ ሙኅዲን (ተከላካይ) ፣ አቤንኤዘር ሲሳይ (አማካይ) ፣ ፍራኦል ጫላ (አጥቂ) እና ነቢል ኑሪ (አጥቂ) በማሳደግ በፕሪምየር ሊጉ የመጫወት ዕድል መስጠቱ አይዘነጋም፡፡
ከክለቡ ጋር በተያያዘ በረዳት አሰልጣኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ከክለቡ ጋር እንደማይቀጥሉ ለማወቅ የቻልን ሲሆን ሌላኛው ረዳት አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ግን ከክለቡ ጋር እንደሚቀጥል ሰምተናል፡፡