በአቋም መፈተሻ ጨዋታ ነገ ዋልያዎቹን የሚገጥመው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ከቀትር በኋላ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።
በህመም ምክንያት ዋና አሠልጣኙ ጆን ኬይስተርን ሳይዝ ከትናንት በስትያ አዲስ አበባ የደረሰው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ትናንት ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ባህር ዳር እንዳቀና ይታወቃል። ቡድኑም ባህር ዳር ከደረሰ በኋላ በባህር ዳር ስታዲየም የመለማመጃ ሜዳ ቀለል ያለ ልምምድ አመሻሽ ላይ አድርጎ ነበር። በአጠቃላይ 40 የልዑካን ቡድን ይዞ በመምጣት በኦሊቭ ሆቴል ማረፊያውን ያደረገው ስብስቡም ነገ ጨዋታውን ከማድረጉ ከ24 ሰዓት በፊት በዋናው ስታዲየም ለ1:20 የቆየ ልምምድ ሰርቷል።
ሦስት የግብ ዘቦችን እና ሀያ የሜዳ ላይ ተጫዋቾችን በአጠቃላይ ሀያ ሦስት ተጫዋቾች የያዘው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻ የልምምድ መርሐ-ግብሩ ቀለል ያሉ ሥራዎችን ሲሰራ ተመልክተናል። በቅድሚያም ተጫዋቾቹ ካፍታቱ በኋላ ፈጣን እንቅስቃሴ የታከለበት የሩብ ሜዳ መሐል ባልገባ ሲሰሩ ነበር። ከዚህ የተለመደ ነገርግን ፈጣን የቦታ እና የሰው ልውውጦቹ በነበረበት የልምምድ መርሐ-ግብር በኋላ ደግሞ ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ ሙሉ ሜዳ ጨዋታ አድርጓል።
ሠላሳ ደቂቃ በፈጀው የሙሉ ሜዳ ጨዋታ ላይም የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኞች ተጫዋቾቻቸው የመስመር ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ሲመክሩ እንዲሁም አቅጣጫ ሲያሳዩ አስተውለናል። ይህ የተግባር ስራ ካበቃ በኋላ ደግሞ ተጫዋቾቹ የቆመ ኳስ እንዲለማመዱ ተደርጓል። በዚህም ያን ያህል በቁመታቸው ዘለግ ያላሉት የቡድኑ ተጫዋቾች ከመዓዘን ምት እና ከቅጣት ምት ኳሶችን ወደ ግብነት እንዲቀይሩ ሲለማመዱ ነበር። 10:05 ሲልም ልምምድ ሊሰራ ለመጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሜዳውን አስረክበው ወጥተዋል።