በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመዲና ዐወል ሦስት እና በሎዛ አበራ ተጨማሪ ጎል ቪጋ ኪዊንስን 4ለ2 በመርታት የመጀመሪያ ታሪካዊ ድሉን አስመዝግቧል፡፡
ታንዛንያዊቷ የመሐል ዳኛ ሰሚራ ናባዳ በመራችው በዚህ ጨዋታ ጠንከር ያለ ፉክክርን ለመመልከት ችለናል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ንግድ ባንክ ኳስን በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የታየ ቢሆንም ከፊት ያሉ አጥቂዎችን ሊረዱ የሚችሉ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች በአግባቡ ተጠግተው አለመጫወታቸው አብዛኛዎቹ የቤት ሥራዎች በሦስቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጓል ማለት ይቻላል። ተጋጣሚው ቪሂጋ በሜዳው እንደመጫወቱ ንግድ ባንክን በእንቅስቃሴ መፈተን ያልቻለ ሲሆን በቆመ ኳስ ላይ የነበራቸው አጠቃቀም ጎሎች እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡
ገና 2ኛው ደቂቃ ላይ በተደጋጋሚ በግራ በኩል ታሪኳ ዴቢሶን ስትፈትን የነበረችው ጄትሪክ ሺጋንግዋ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርራ መታ በግቡ የላይኛው ቋሚ ብረት ለጥቂት የወጣባትን ኳስ የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጎል በማስቆጠሩ ረገድ ቀዳሚ የሆኑት ንግድ ባንኮች ናቸው፡፡ 9ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል አረጋሽ ካልሳ እግሯ ላይ የደረሰውን ኳስ በፍጥነት ለሎዛ ሰጥታት አጥቂዋም በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረችው መዲና ዐወል አሳልፋላት ዘንድሮ መከላከያን ለቃ ክለቡን የተቀላቀለችው ተጫዋቿ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ክለቧን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡
በሁለቱም የባንክ ኮሪደሮች ግቦችን ለማግኘት የሚመስል ፈጣን እንቅስቃሴን ሲያሳዩ የነበሩት ቪጋ ኪዊንሶች በፔሊስቱሳ ካዳሪ እና ጄትሪክስ ሺካንጎዋ አማካኝነት ወደ ጎል መቅረብ ችለዋል፡፡ ተሬዛ ኢንገሻ ከርቀት መታ ታሪኳ በርገና ካወጣችባት በኋላ ሁለት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ አቻ የሆኑበትን ጎልም አግኝተዋል፡፡ 11ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ፔሊስቱሳ ካዳሪ ስታሻማ ህይወት ደንጊሶ በግንባር ብትገጭም በአግባቡ ኳሱ ባለመራቁ ማውሪን አቼንግ እግር ስር ገብቶ አጥቂዋም በቀላሉ ከመረብ አሳርፋ ቡድኗን አቻ አድርጋለች፡፡
ጨዋታው ቀጥሎ 21ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ የሜዳ ላይ ቆይታ የነበራት መዲና ሁለተኛውን ጎል በማስቆጠር ንግድ ባንኮችን በድጋሚ ወደ መሪነት አሸጋግራለች፡፡ ሎዛ አበራ ከተመሳሳይ ቦታ በተመሳሳይ ሒደት ያቀበለቻትን ኳስ መዲና የቪጋ ኪዊንሷን ግብ ጠባቂ ሊሊያን አውርን አልፋ አስቆጥራዋለች፡፡
ግብ ያስቆጥሩ እንጂ በመከላከሉ ረገድ ዝንጉነት ይታይባቸው የነበሩት ንግድ ባንኮች አሁንም ከቆመ ኳስ በቀላሉ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። 37ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ በቪጋ ኪውንስ ተጫዋች ላይ ጥፋት ፈፅመሻል በማለት የዕለቱ ዳኛ የሰጠችውን የቅጣት ምት ድንቅ እንቅሴቃሴ በማድረግ የባንክ ተከላካይን ስትረብሽ የነበረችው ጄትሪክ ሺካንጎዋ አክርራ ወደ ግብ ስትመታ ታሪኳ በርገና በመትፋቷ ማውሪን አቼንግ ጋር ደርሶ በድጋሚ ቡድኗን አቻ በማድረግ 2ለ2 በሆነ ውጤት አጋማሹ ተገባዷል፡፡
ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ንግድ ባንኮች በይበልጥ የግብ መጠናቸውን ማሳደግ የቻሉበት አጋማሽ ነበር። በተለይ የሎዛ አበራ እና መዲና ዐወል ጥሩ የመናበብ ሂደት ለቡድኑ ውጤታማነት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በአንፃሩ ቪጋ ኪዊንሶች ከተሻጋሪ ከቆሙ ኳሶች በተለይ በጄትሪክ ሺካንጎዋ አማካኝነት ልዩነት ለመፍጠር ጥረት አልተለያቸውም፡፡ 48ኛው ደቂቃ በንግድ ባንክ የግብ ክልል አካባቢ የተገኘውን ቅጣት ምት ጀትሪክ አክርራ መታ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት የዚህኛው አጋማሽ ቀዳሚው ቪጋዎች ያደረጉን ሙከራ ነበረ፡፡ 61ኛው ደቂቃ ላይ ጀትሩክ አንድ ለአንድ ከታሪኳ በርገና ጋር ተገናኝታ በሚገርም ብቃት ታሪኳ ያወጣችባት ሌላኛው አስቆጭ የቡድኑ ሙከራ ነች፡፡ በተመሳሳይ ጀትሪክ ከርቀት በሌላ አጋጣሚ አክርራ መታ ታሪኳ ያወጣችባት የቪጋ ኪዊንሶች ተጨማሪ ሙከራም ነበረች፡፡
በሂደት ይበልጥ በአጥቂ ክፍላቸው ላይ ስልነት እየታየባቸው የመጡት የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ልጆች በተለይ ሎዛ እና መዲና የፈጠሩት ጥምረት ሁለት ተጨማሪ ጎሎች እንዲያስቆጥሩ አስችሏቸዋል፡፡በ69ኛው ደቂቃም ሎዛ አበራ በማቀበሉ መዲና ዐወል ወደ ጎልነት በመቀየሩ ሐት ትሪክ ሰርተው ባንክን ወደ መሪነት አሸጋግረዋል፡፡
84ኛው ደቂቃ ላይ መዲና ዐወል የግል አቅሟን በአግባቡ ተጠቅማ ለሎዛ አበራ ሰጥታት አምበሏ አራተኛ እና የማሳረጊያዋን ጎል ከመረብ አዋህዳ ጨዋታው 4ለ2 በሆነ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡
በታሪክ የመጀመርያውን የመድረኩን ጨዋታ ያከናወነው የንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን በጣፋጭ ድል ጉዞውን ከመጀመሩ በተጨማሪ ለቡድኑ የመጀመርያ ጨዋታዋን ያከናወነችው መዲና ዐወል ሐት ትሪክ ሰርታ የውድድሩ ባለታሪክ ሆናለች።
በዚሁ ምድብ ቀደም ብሎ በተደረገ ጨዋታ ዪይ ጆይንት ስታርስ ከ ኒው ጀነሬሽን ተገናኝተው ጆይንት ስታርሶች በማኩንዳ ጆሴፍ እና ሉካ ዲቦራ ጎሎች 2ለ1 አሸንፈዋል፡፡