በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ አመሻሽ በዋቢሸበሌ ሆቴል የሽኝት ፕሮግራም ተከናውኖለታል፡፡
የአፍሪካ ሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ በግብፅ መዲና ካይሮ በስምንት ክለቦች መካከል ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆኖ ለመገኘት ቀደም ብሎ ክለቦች በያሉበት ቀጠና የማጣሪያ ጨዋታዎች ማድረግ እንዳለባቸው ካፍ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በሴካፋ ዞን በሚገኙ ክለቦች መካከል ከፊታችን ቅዳሜ ነሀሴ 22 ጀምሮ በኬንያ ውድድራቸውን ማድረግ ይጀምራሉ፡፡
ለዚህ ውድድር ከኢትዮጵያ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአርባ ቀናት ያህል በቢሾፍቱ ከተማ መቀመጫውን በማድረግ ልምምዱን ሲያከናውን ቆይቶ በነገው ዕለት ሀሙስ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ረፋድ 5፡00 ወደ ኬንያ ያቀናል፡፡ ለዚህሞ በዛሬው ዕለት አመሻሽ አዲስ አበባ በሚገኘው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ለክለቡ የልዑካን አባላት የአሸኛኘት ስነ ስርአት ተከናውኖላቸዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ፕሬዝዳንት አቶ አቢ ሳኖ እና የስፖርት ክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዓሊ አሕመድ እንዲሁም የክለቡ የተለያዩ አመራሮች አሰልጣኞች እና አጠቃላይ የቡድኑ ተጫዋቾች ተገኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበርም በሥፍራው ተገኝቶ ቡድኑን አበረታቷል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቢ ሳኖ ለቡድኑ አባላት የመልካም ምኞታቸውን ባደረጉት ንግግር መሀል የገለፁ ሲሆን “በውድድሩ ስኬታማ ቡድን ሆኖ እንደሚታይም አልጠራጠርም” በማለትም ገልጸዋል፡፡በመቀጠል የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው እና አምበሏ ሎዛ አበራ የተቀበሉትን አደራ በአግባቡ ተወጥተው ለመምጣት እና ከክለቡ ባሻገር ሀገር ለማስጠራት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም የባንኩ ፕሬዝዳንት እና በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማኅበር የአርማ ፣ የአበባ እና የሰንደቅ አለማ ስጦታ ለክለቡ አሰልጣኝ እና አምበል ካበረከቱ በኋላ ፕሮግራሙ በፎቶ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡
ነገ ወደ ውድድሩ ስፍራ የሚያመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአራት ቀናቶች በኋላ ዕለተ ሰኞ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ከኬንያው ክለብ ቪጋ ኩዊንስ ጋር በማድረግ ይጀምራል፡፡
ከአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ጋር ያደረግነውን ቆይታ ከቆይታዎች በኋላ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል፡፡