ከሰዓታት በኋላ ከሴራሊዮን አቻው ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ አሰላለፍ ታውቋል።
በ2022 በኳታር አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ውድድር ለመብቃት ከፊቱ ያሉበትን የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ማለፍ የሚጠበቅበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማጣሪያው ከጋና እና ዚምባብዌ ጋር ላሉበት የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዎች ከነሐሴ 4 ጀምሮ ልምምድ ሲሰራ እንደቆየ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑም ወሳኞቹን ጨዋታዎች በተሻለ አቅም ለመቅረብ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ያገኘ ሲሆን ዛሬ ዘጠኝ ሰዓትም ከሴራሊዮን ጋር የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በዚህ ጨዋታ የሚጠቀሙትን የመጀመርያ አሰላለፍም ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታለች።
ተክለማርያም ሻንቆ በግብ ብረቶቹ መካከል የሚቆም ግብ ጠባቂ ነው። ከተክለማርያም ፊት ደግሞ ረመዳን የሱፍ፣ አስቻለው ታመነ፣ ያሬድ ባዬ እና ሱሌይማን ሀሚድ የቡድኑ አራት ተከላካዮች ሲሆኑ ይሁን እንዳሻው፣ መስዑድ መሐመድ እና ታፈሠ ሰለሞን በበኩላቸው የአማካይ መስመሩ ላይ የሦስትዮች ጥምረት ፈጥረው ወደ ሜዳ የሚገቡ ተጫዋቾች መሆናቸው ታውቋል። ሱራፌል ዳኛቸው እና ሽመክት ጉግሳ ደግሞ የመሐል አጥቂውን አማኑኤል ገብረሚካኤልን ግራ እና ቀኝ በማጀብ የቡድኑን የፊት መስመር የሚመሩት ይሆናል።