ያለ ግብ ከተጠናቀቀው የኢትዮጵያ እና ሴራሊዮን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ውበቱ አባተ – ኢትዮጵያ
ጨዋታው እንዴት ነበር?
የዛሬው ጨዋታ ለሁሉም ተጫዋቾች በጣም ወሳኝ ነበር። ምክንያቱም አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ጨዋታ የመጡት ስለነበር። ከዚህ አንፃር ጨዋታው መጥፎ አልነበረም። በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ጨዋታውን ለመቆጣጠር ችለናል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልልም በምንችለው መንገድ ለመግባት ሞክረናል። እንዳልኩት ግን ለረጅም ጊዜ ከጨዋታ ርቀን እንደመምጣታችን ያሳየነው እንቅስቃሴ መጥፎ አይደለም። ምናልባት ግን የግብ ዕድሎችም የመፍጠሩ ረገድ ላይ የበለጠ መስራት አለብን። ከዚህ ውጪ ግን አጠቃላይ የነበረው እንቅስቃሴ መልካም ነው።
በሚፈለገው ልክ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ስላለመፍጠራቸው…?
በጨዋታው ሙሉ ለሙሉ የግብ ማግባት ዕድሎችን አልፈጠርንም ማለት ሳይሆን በምንፈልገው ልክ አብዝተን አልፈጠርንም ነበር። በአንፃራዊነት በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ አጋጣሚዎችን ፈጥረን ነበር። የተሻለ ዝግጁነት ስላልነበረን ግን የነበሩትን ዕድሎች አልተጠቀምንባቸውም። ግን ከዚህ በላይ ግብ ማስቆጠር የምንችልበት እንቅስቃሴ ማሳየት እንዳለብን ይሰማኛል። የነበረን አጠቃላይ ብልጫ በጎል ቢታጀብ ጥሩ ነበር። በቀጣይ ይህንን ለማስተካከል እንሰራለን።
የዛሬው ጨዋታ ጥቅም…?
ከጨዋታ በጣም ስለራቅም ወደ ጨዋታ ሪትም ለመግባት በጣም ይጠቅመናል። ስለዚህ በጨዋታው የተጫዋቾቹን የአካል ብቃት በደንብ ለይተንበታል። ይህ ቡድን ለጋናው ጨዋታ ብቻ አይደለም የሚዘጋጀው። እስከ አፍሪካ ዋንጫው ድረስ ጥሩ ቡድን እንዲመስል ነው እየሰራን ያለነው። ከዚህ አንፃር መጫወት የምንፈልገውን ነገር እያገኘን እንደሆነ ይሰማኛል። ቡድኑ ውስጥ ጉድለቶች አሉ። በቀጣይ ግን ጉድለቶቹን እያስተካከልን ከሄድን ጠንካራ ቡድን ይኖረናል። የጋናው ጨዋታ የቅርብ ጊዜ እቅዳችን ነው። ዋናው አላማችን ለትልቁ ድግስ (አፍሪካ ዋንጫ) ቡድኑን ማዘጋጀት ነው።
ስለጌታነህ ከበደ ጉዳት…?
ጌታነህ የጡንቻ ጉዳት ነው ያጋጠመው። ጉዳቱ ምን ያህል እንደሚያቆየውም እርግጠኛ አይደለሁም። ከህክምና ቡድን አባላቶቼ ጋርም ያለውን ነገር እየተከታተልን ነው። በቅርቡም ለጨዋታ ብቁ እንደሚሆን እገምታለሁ። በእሁዱ ጨዋታም የተወሰነ ደቂቃ ይሞክራል ብዬ አስባለሁ።
አሚዱ ካሪም – ሴራሊዮን (ምክትል አሠልጣኝ)
ስለ ጨዋታው…?
በመጀመሪያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታውን ስላመቻቸ ማመስገን እፈልጋለሁ። ወደ ጨዋታው ስመለስ ጥሩ ለመጫወት ሞክረናል። ከኢትዮጵያ ጋር ከዚህ ቀደም ተጫውተን እናውቃለን። በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሀዋሳ ላይ ስንጫወት እኔው ምክትል ስለነበረወኩ የቡድኑን የጨዋታ መንገድ አይቼ ነበር። ቡድኑ ከኳስ ጋር ብዙ ጊዜውን ስለሚያጠፋ ወደ ኋላ አፈግፍገን ቦታዎችን መዝጋት እንዳለብን ተነጋግረን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። አለበለዚያ እንደምንቀጣ አውቅ ነበር። ይህ ስልታችን ሰርቶም አንድ ነጥብ ተጋርተን ወጥተናል።
ስለተጋጣሚያቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቃት እና መከላከልን ስለመረጡበት ምክንያት…?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጣም ጥሩ ቡድን ነው። እንዳልኩት ኳስን ማንሸራሸር የሚወድ ቡድን ነው። ተጫዋቾቹ ለረጅም ደቂቃ ኳስን መቀባበል ይችላሉ። እኛ ይህ አይነት ብቃት የለንም። እኛ በደንብ ወደ ኋላ አፈግፍገን ስለነበር ስንጫወት የነበረው ሰብረውን መግባት አልቻሉም ነበር። ተጫዋቾቹን ወደ ፊት ገፍተን ብንጫወት ኖሮ ግን በደንብ እንደምንቀጣ አውቅ ነበር። ስለዚህ ኳሱን ትተንላቸው መከላከልን መረጥን።
ውጤቱ ፍትሃዊ ነው?
ለእኛ ፍትሃዊ ነው። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግን ፍትሃዊ አይመስለኝም። ግን እኛ አቻ በመውጣታችን ደስተኞች ነን።