የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ውድድር የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

በባቱ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ውድድር የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው የተለያዩ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በሼር ሜዳ የምድባቸው የመጀመርያ ጨዋታቸውን በድል የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ተገናኝተው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። እጅግ ጠንካራ ፉክክር ያስመለከተን ይህ ጨዋታ ክለቦቹ በታዳጊ ላይ በቂ የሆነ ስራ እየሠሩ መሆኑን እንቅስቃሴያቸው ያረጋግጣል። ጥቂት የጎል ሙከራዎች በተመለከትንበት በዚህ ጨዋታ ጥቂቱንም ሙከራ ቢሆን ወላይታ ድቻዎች አድርገውታል። የተደራጀ አጨዋወት የሚጫወቱት ድቻዎች በመጀመርያው አጋማሽ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አጥቂው መሳይ መለሰ ወደ ጎል ነት ቀይሮታል። ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረው ወደ ፊት ለመሄድ ቢሞክሩም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ካለመረጋጋት የተነሳ የሚያባክኑት ጊዮርጊሶች ጠንካራውን የድቻን የመከላከል አጥር ጥሰው ለማለፍ መቸገራቸው የኳስ ብልጫቸውን ትርጉም አልባ አድርጎባቸዋል።

በዚህ ሒደት ውስጥ ከሠላሳ ሜትር ርቀት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀጥታ በተመታ ኳስ ጎል አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም የዕለቱ ዳኛ ከጨዋታ አቋቋም ውጭ የገባ ጎል ነው በማለት ሳያፀድቅ በመቅረቱ በፈረሰኞቹ በኩል ቅሬታ አስነስቷል።

ከእረፍት መልስ በተመሳሳይ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ የቆዮት እና የወላይታ ድቻን የመከላከል አጥር ማለፍ የከበዳቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊዎች በመጨረሻም ጥረታቸው ተሳክቶ እጅግ ግሩም ጎል ከአስራ ስድስት ከሀምሳ ውጭ በረከት በቀለ አስቆጥሮ ጨዋታው አንድ አቻ ተጠናቋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በይድነቃቸው ተሰማ ውድድር ከዚህ ቀደም ያየነው አጥቂው አሮን ኢንተሎ እና ሌላኛው ተጫዋች ዳግም ፍቃዱ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አስመልክተውናል። በወላይታ ድቻ በኩል ከመስመር እየተነሳ ፈጣን እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየው አንበሉ መሳይ መለሰ የሚያድግ አቅም እንዳለው ታዝበናል።

አምስት ሰዓት በቀጠለው የሼር ሜዳ ሁለተኛ ጨዋታ ሲዳማን ከ ሱማሌ አገናኝቶ በመጀመርያ አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን አስመልክቶናል። ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ሲዳማዎች በዕለቱ ድንቅ እንቅስቃሴ ባደረገው አጥቂው ይደግልኝ አስፋው አከታትሎ ባስቆጠረው ሁለት ጎሎች መምራት ችለዋል። ምንም እንኳን በየጨዋታው ጎሎች ይቆጠርባቸው እንጂ ጥሩ እግርኳስ መጫወት የቻሉት ሶማሌዎች በሲዳማ ተከላካዮች ሳጥን ውስጥ ተደራርቦ የቀረውን ኳስ በአብዱልቃድር አሊ አማካኝነት በማስቆጠር መነቃቃት ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የሲዳማን የበላይነትን ያስመለከተ ሲሆን ከማዕዘን ምት የተሻገረውን መልካሙ ማትዮስ በግንባሩ ገጭቶ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። የኃይል አጨዋወት መብዛት ምክንያት የጨዋታውን እንቅስቃሴ እየቆራረጠ በቀጠለው ጨዋታ አብዲሀኪም ሁሴን ግሩም ጎል አስራ ስድስት ከሀምሳ ጠርዝ ላይ በማስቆጠር የሱማሌን የጎል መጠን በማጥበብ በቀሪው ደቂቃዎች ሲዳማን ማስጨነቅ ቢችሉም የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በሲዳማ 3-2 አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል።

በሱማሌ በኩል አብዲሀኪም ሁሴን እና ሀምዚ አብዲ ተስፋ የሚጣልባቸው ተጫዋቾች ናቸው።

የምድብ ሐ ጨዋታ ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ እኩል አራት ነጥብ ሲይዙ ሲዳማ ሦስት ነጥብ በመያዝ ሦስቱም ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድላቸውን በመጨረሻው ጨዋታ ይጠብቃሉ። ሶማሌ ሁለት ተከታታይ ጨዋታ በመሸነፉ ለመርሀግብር ማሟያ ካልሆነ በቀር ከውድድር ውጭ መሆኑን አረጋግጧል።

በባቱ ሜዳ የተካሄደው የኢትዮጵያ ቡና እና ደቡብ ጨዋታ ያለጎል ሲጠናቀቅ በጨወዋታው ወቅት ከተጫዋች ጋር የተጋጨው የደቡቡ ተከላካይ ዕዝራ ማትዮስ ከበድ ያለ ጉዳት አጋጥሞት በስፍራው የነበረው የስፖርት ቤተሰብ ያስደነገጠ ቢሆንም ለተሻለ ህክምና ካመራ በኃላ በመልካም ጤንነት እንደሚገኝ አረጋግጠናል።

በዚሁ ምድብ በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ተገናኝተው ሁለት አቻ ተጠናቋል። ባህር ዳሮች በፋይሰል አህመድ ጎል ቀዳሚ የነበሩ ቢሆንም ግሩም ዳንኤል እና ሰለሞን ግርማ ለወልቂጤ አከታትለው በማስቆጠር ሠራተኞቹ መሪ ሆነው የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል። ከዕረፍት መልስ ዳንኤል ደጀን ለባህር ዳር የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ጎልነት በመቀየር ጨዋታው በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በምድብ ለ ኢትዮጵያ ቡና እና ደቡብ አራት ነጥብ ሲኖራቸው ወልቂጤ እና ባህር ዳር አንድ አንድ ነጥብ ይዘዋል። በሂሳባዊ ስሌት ከዚህ ምድብ ወደ ሩብ ፍፃሜው ያለፈው ቡድን ያልታወቀ በመሆኑ የመጨረሻውን ጨዋታ መጠበቅ አስፈላጊ ሆኗል።

የምድብ መ ሁለት ጨዋታ ከሰባት ሰዓት በኃላ ሲካሄድ ሀዋሳ ከተማ ሐረሪን ከጨዋታ ብልጫ ጋር 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ጎሎቹንም በጨዋታ አማኑኤል ሞገሰ ሁለት አንዷን ጎል ያብስራ አስደሳች በማስቆጠር ጨዋታው ተጠናቋል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የአርባምንጭ እና የድሬዳዋ ሲያገናኝ አርባምንጮች በሁሉም ረገድ ብልጫ በመውሰድ 3-0 አሸንፈዋል። ጎሎቹን ዮርዳኖስ ኢያሱ፣ ቴዎድሮስ አጬ እና በኃይሉ ንጋቱ አስቆጥረዋል።

በአርባምንጭ በኩል አጥቂው ዮርዳኖስ ኢያሱ እና ቢንያም ንጉሡ ጥሩ የሚያድግ አቅም እንዳላቸው ተመልክተናል።

በምድብ መ ሀዋሳ እና አርባምንጭ አራት ነጥብ ሲኖራቸው ሐረሪ ሦስት ነጥብ ይዞ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት የመጨረሻ ጨዋታቸውን ይጠብቃሉ። ድሬዳዋ ደግሞ ከወዲሁ ከውድድሩ ውጭ መሆኑን አረጋግጧል።

በውድድሩ ላይ ከተመለከትናቸው ዳኞች መካከል የመሐል ዳኛዋ ዮርዳኖስ ሙሉጌታ ራሷን ማሳደግ ከቻለች ወደ ፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው ዳኞች መካከል አንዷ ልትሆን እንደምትችል ታዝበናል።


ተጨማሪ ምስሎች እና የቀጣይ መረጃዎችን በማኅበራዊ ገፆቻችን ያገኛሉ።