ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኬንያ ገብቷል

ለአፍሪካ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ለመብቃት የቀጠናውን የማጣሪያ ውድድር ማሸነፍ የሚገባው ንግድ ባንክ ፍልሚያውን ወደሚያደርግበት ሀገር ዛሬ ቀትር አምርቷል።

በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጣይ ዓመት በሚደረገው የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት ሲያደርግ እንደከረመ ይታወቃል። በኬንያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው እና በዋናው ውድድር ተሳታፊ የሚሆነውን ክለብ የሚለየው የቀጠናው ፍልሚያ ደግሞ ከነሐሴ 22 እስከ ጿጉሜ 4 ድረስ እንደሚከናወን ይታወቃል።

ለዚህ የዞኑ ፍልሚያ ከሰኔ 25 ጀምሮ ቢሾፍቱ ላይ ልምምዱን ሲሰራ የነበረው ክለቡም ዛሬ ቀትር ወደ ስፍራው መጓዙ ታውቋል። ለሁለት ሰዓት የተጠጋ በረራ አከናውኖ 7:30 ሲል ኬኒያ የደረሰው ልዑካን ቡድኑም በፌርቪው ሆቴል ማረፊያውን እንዳደረገ ለማወቅ ችለናል።

አጠቃላይ 28 የልዑካም ቡድን (21 ተጫዋቾች) በመያዝ ወደ ስፍራው ያመራው ስብስቡም ነገ በጂምካና የመለማመጃ ሜዳ የመጀመሪያ ልምምዱን ለአንድ ሰዓት ተኩል ያክል እንደሚሰራ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። በተመሳሳይ በጂምካና ሜዳ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ልምምዱ ከሰራ በኋላም እሁድ ነሐሴ 23 ከቪሂጋ ኩዊንስ ጋር የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን የሚያከናውን ይሆናል።


ያጋሩ