ዐፄዎቹ ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደርጋሉ

በመስከረም ወር ለሚጠብቃቸው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች ነገ ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር አሸናፊ የሆኑት ፋሲል ከነማዎች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመካፈል የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ከመስከረም ወር ጀምሮ እንደሚያከናውኑ መገለፁ ይታወቃል። በመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ መርሐ-ግብር ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር የተደለደለው ክለቡም ከሐምሌ 5 ጀምሮ ባህር ዳር ላይ መቀመጫውን በማድረግ ልምምዱን ሲሰራ ከርሟል። አሁን የተገኘው መረጃ ደግሞ ክለቡ ከዋልያዎቹ ጋር እሁድ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ከመጣው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያደርግ ይጠቁማል።

በትናንትናው ዕለት ባህር ዳር የደረሰው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ፋሲሎች ያቀረቡለትን ጥያቄ መቀበሉን ያረጋገጥን ሲሆን ጨዋታውም ነገ 9 ሰዓት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚከናወን ተረድተናል። ለተመልካች ዝግ የሆነውን ጨዋታም ኢንተርናሽናል ዳኞች እንዲመሩት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ለወትሮ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ ሲሰራ የነበረው የአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ስብስብም የነገውን ጨዋታ ታሳቢ በማድረግ ዛሬ ረፋድ ለአንድ ሰዓት ከ10 ደቂቃዎች ያክል የቆየ ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሲሰራ አስተውለናል።