የካፍ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ ተጀምሯል

በኬንያ አስተናጋጅነት በስምንት የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች መካከል የሚደረገው የካፍ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ በሁለት መርሐግብር ተጀምሯል፡፡

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግን በስምንት ክለቦች መካከል በግብፅ ካይሮ ለማሰናዳት እቅድ ይዟል፡፡ ለዚህም ውድድር ይረዳ ዘንድሮ ቀደም ብሎ ካፍ ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት ክለቦች በያሉበት ቀጠና የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታን ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ይህ ውድድርም በዛሬው ዕለት በኬንያ አስተናጋጅነት በሁለት ጨዋታዎች በናይሮቢ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በኒያዮ ስታዲየም 7፡00 ሲል በምድብ አንድ የሚገኙት የዩጋንዳው ሌዲ ዶቭስ እና የጅቡቲው ኤፍኤዲ በመክፈቻ ጨዋታ ተገናኝተው ሌዲ ዶቭስ 5ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ኢትዮጵያዊያኗቹ መዳብ ወንድሙ በመሐል ዳኝነት፣ ወይንሸት አበራ እና ይልፋሸዋ አየለ በረዳት ዳኝነት እና አስናቀች ገብሬ በአራተኛ ዳኝነት በመሩት ጨዋታ ሪቲሺያ ናቦቦሳ ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር ፋዚላ ኢኩዋፑት ፣ አሉፕ ኖርሀ እንዲሁም ደግሞ የኤፍኤዲ ተከላካይ ናስቲኦ ሮብሌ በራሷ ላይ ለዩጋንዳው ክለብ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡

ቀጥሎ 10፡00 ሲል ከዚሁ ምድብ አንድ ላይ የተደለደሉት ፒቪፒ እና ሲምባ ክዊንስ ተገናኝተው የታንዛኒያው ሲምባ ክዊንስ ድል ቀንቶታል፡፡ 4ለ1 በሆነ ውጤት ክለቡ መርታት ሲችል ፍላቪን ሙሶሎ በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምት ሁለት ጎሎችን ቀሪዎቹን ሁለት ጎሎች ደግሞ ዳናይ ቦሆቦሆ እና አይሻ ሙኑካ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ብቸኛውን የፒቪፒ ግብን ናስራ ናሂማና ከመረብ አዋህዳለች፡፡

ኢትዮጵያን የወከለው የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተደለደለበት የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ነገ ዕሁድ ይካሄዳሉ፡፡ 7፡00 የደቡብ ሱዳኑ ዬይ ጆይንት ስታርስ ከ ዛንዚባሩ ኒው ጀነሬሽን ሲጫወት 10፡00 ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቪጋ ኪውንስ ጋር ጨዋታቸውን ይከውናሉ፡፡