ከሰሞኑን መነጋገርያ ርዕሰ ጉዳይ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ምክትል አሰልጣኝ ጉዳይ ወደ ፌዴሬሽኑ አምርቷል።
ያለፈውን አንድ ዓመት የአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ ምክትል በመሆን ያገለገለው አሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ በክለቡ አስተዳደራዊ ውሳኔ መሠረት በሥራ ገበታው ላይ እንደማይገኝ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም ዋና አሠልጣኙ የምክትሉ ኮንትራት እንዲራዘም እና ረዳቱ ሆኖ እንዲቀጥል መጠየቁ ይታወሳል። ሆኖም ክለቡ ጉዳዩ እየታየ አሠልጣኝ ካሣዬ ቡድኑን ማሠልጠን እንዲቀጥል አቅጣጫ መስጠቱ የሚታወቅ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሠልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ እና ለክለቡ በደብዳቤ ማሳወቁ ታውቋል። አሠልጣኙ በደብዳቤው “በሥራ ገበታዬ እንዳልገኝ የተደረግኩት በካሣዬ አራጌ የቃል ንግግር መሆኑን እና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ በወቅቱ አሰልጣኝ ካሣዬ ጉዳዩ እየተከታተለ ነበር። ያም ሆኖ ቀናቶች እየገፉ መፍትሔ ሳላገኝ ቀርቻለው። ስለሆነም እስከ ነሐሴ ሠላሳ ኮንትራት ያለኝ በመሆኑ ወደ ሥራዬ መመለስ ይገባኛል። ይህ ካልሆነ ከሥራ ገበታዬ የተነሳሁበት እንዲሁም ወደ ዝግጅት እንዳልገባ የተደረገበት ምክንያት ምን እንደሆነ ክለቡ በፅሁፍ ማብራርያ ይስጠኝ።” በማለት ገልጿል።