የፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ እየተደረገ ይገኛል።

መገኘት ከነበረባቸው 16 ክለቦች የ12 ክለብ ተወካዮች በተገኙበት በዚህ ጉባዔ ላይ የማኅበሩ ሰብሳቢ መቶ ዓለቃ ፈቃደ ማሞ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የተለያዩ ሀሳቦችንም በዚህ መልኩ አንስተዋል።

” በቅድሚያ መከላከያ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ሊጉን ስለተቀላቀላችሁ እና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አባል ስለሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ።

” ከሱፐር ስፖርት ጋር በመተባበር በብራንዲንግ ዙርያ የሁለት ቀን ወርክሾፕ ሰጥተናል። ይህ ስልጠና ለተሳታፊዎች እጅግ ጠቃሚ ነበር። ሴፕቴምበር ላይ ደግሞ ሰፋ ያለ የ15 ቀናት የአሠልጣኞች ስልጠና እንሰጣለን። ሥልጠናውን የሚሰጡት ከሆላንድ የሚመጡ በቂ እውቀት ያላቸው ናቸው። በዚህ አጋጣሚ አሠልጣኞቻችሁን እንድትልኩልን። ሌላው ማኅበሩ ያስቀመጣቸው አላማዎችን፣ ከክለቦች ጋር ያለውን ግንኙነት እና ከፌዴሬሽኑና ሌሎች አካላት ጋር የሚኖረንን ግንኙነት የሚመረምር የጥናት ቡድን አቋቁመናል። አሁን ሦስተኛ የጥናት ደረጃ ላይ ደርሷል። በጥብቅ የማሳስበው የክለብ አመራር ስማችሁ ለኮንሰልታንቶች ተላልፏል። ሲደውሉላችሁ እባካችሁ ምላሽ ስጧቸው። የማታቁትን ስልክ አታነሱም፤ የቢሮ ስልክም ብዙ ጊዜ አይነሳም። ጥናቱ ሊጉን ከሌሎች አካላት ጋር ያለውን አንድነት እና ልዩነት በፊፋ ደንብ መሠረት የምንወስንበት ስለሆነ ትብብር እንድታደርጉላቸው።

” በ2014 ብዙ እቅዶች አሉን። ከዐምናው በተሻለ ሁኔታ ለመፈፀም በኛ በኩል ዝግጅቱ ተጠናቋል። የሚቀረን ደግሞ ከአቅም ጋር የሚሄድ ነው። ትልቅ ችግር የሚሆነው የሚያስተናግዱ ሜዳዎች ላይ በቂ መብራት አለ ወይ የሚል ከፍተኛ ጥያቄ አለ። በሱፐር ስፖርት በኩል የሚተላለፉ ጨዋታዎች ጥሩ እንዲሆኑ በምሽት ቢካሄድ ይሻላል የሚል ሀሳብ አለ። ግን ስታዲየሞቻችን የሲሚንቶ ክምር እንጂ ለእግርኳስ የተዘጋጁ አይደሉም። ትልልቆቹ ሜዳዎቹ ጭምር የመብራት ችግር አለባቸው። በዚህ ዙርያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያካሄድን ነው። አቅም ይጠይቃል፤ ሆኖም በተቻለ መጠን ይህን ለማሟላት ጥረት እናደርጋለን። “