የቀጣይ ዓመት የሊጉ ውድድር የሚደረጉባቸው ስታዲየሞች በቅደም ተከተል ታውቀዋል

በአስራ ስድስት ክለቦች መካከል የሚደረገውን የ2014 የሊጉን ውድድር የሚያስተናግዱ ስታዲየሞች ዝርዝር ከነቅደም ተከተላቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በአሁኑ ሰዓት ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። በጉባኤው ላይ የሚነሱ ሀሳቦችን ከስር ከስር ወደ እናንተ እያደረስን ሲሆን አሁን ደግሞ የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የቀጣይ ዓመት የሊጉን ውድድር የሚያስተናግዱ ስታዲየሞችን ዝርዝር በተመለከተ ያሉትን እንዲህ አቅርበናል።

” አስፈላጊውን ውይይት አካሂደን ሊጉን በስድስት ከተሞች ላይ ለማካሄድ ወስነናል። ነገር ግን እንደ አስፈላጊነቱ ሊቀየር ይችላል። እንዲሟሉ ያልናቸው ጉዳዮች ካልተሟሉ ወደ ሌሎች ከተሞች እናመራለን። ሀዋሳ የመጀመርያው ምዕራፍ እንዲደረግ አስበናል። በመቀጠል አዳማ ነው የመረጥነው። እንደሚታወቀው አዳማ አዲስ ስለሆነ ብዙ ጥያቄዎች አሉበት። ነገር ግን በቀላሉ ሊሟሉ የሚችሉ ናቸው። ከዛ በመቀጠል በድሬዳዋ እንዲካሄድ ታቅዷል። ከነገ ጀምሮ በሚላክ ደብዳቤ የሚሟሉ ነገሮችን እንገልፃለን። በዛ መሰረት የውድድሩ ጊዜ ሳይደርስ ከተሟላ በፕሮግራሙ መሠረት ድሬዳዋ ላይ ይካሄዳል። በመቀጠል ጅማ፣ ባህር ዳር እና በመጨረሻ አዲስ አበባ ላይ ይካሄዳል። ” ብለዋል።

መቶ አለቃ በገለፃቸው የአዲስ አበባ የማዘጋጀት ጉዳይ ላይ አፅንኦት ሰጥተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ቢጀመርም ቁፋሮ ተከናውኖ መቆሙ፣ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ደግሞ የመጫወቻ ሜዳው (ሰው ሰራሽ ሳር) መጎዳቱ እክል ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመው የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ካልተጠናቀቀ በባህር ዳር ውድድሩ እንደሚፈፀም ገልጸዋል ። ” አዲስ አበባ እንደመዲናነቷ የመክፈቻ እና የመዝጊያው ማዘጋጀት ይገባት ነበር። ነገር ለስታዲየም እንክብካቤ ያለው ግምት አነስተኛ ነው። የአዲስ አበባ ሰታዲየም በሚሰጠው ቀነ ገደብ መስፈርቱን ካላሟላ በባህር ዳር የውድድር ዘመኑን እንጨርሳለን።”

ያጋሩ