በግብፅ ሊግ መድመቅ የቻለው ኢትዮጵያዊው ሽመልስ በቀለ አዲስ አበባ ገብቷል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ሳምንት ላለባት ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣረያ ጨዋታ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ ያቀረቡለት ሽመልስ በቀለ ዛሬ አዲስ አበባ መግባቱን ከሽመልስ ጋር ባደረግነው አጭር ቆይታ አረጋግጠናል።
ነገ ማለዳ በመጀመርያው በረራ ከአዲስ አበባ በመነሳት ወደ ባህር ዳር የሚያቀናው ሽመልስ በቀለ ዘጠኝ ሰዓት በሚደረገው የዩጋንዳ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንደሚደርስ ለማወቅ ችለናል።
በግብፅ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ቡድኑ ምስር ከስሞሀ ጋር አንድ አቻ ሲለያይ ወደ ኢትዮጵያ ባደረገው ጉዞ ምክንያት ያልተሰለፈው ሽመልስ በቀለ ባለደው ሳምንት ባስቆጠራት አንድ ጎል አማካኝነት በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ቁጥር አስራ አንድ በማድረስ የግሉን ሪከርድ ማሻሻል ችሎ ነበር።