በፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ ተመልካቾች እንዲገቡ ተወስኗል

የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በቁጥር የተገደበ ተመልካች ፊት እንዲደረጉ ተወስኗል።

ዛሬ ቀኑን ሙሉ በተከናከነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ላይ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የነበረው ተመልካችን ወደ ስታዲየም የመመለስ ጉዳይ ነበር። ባለፈው ዓመት በኮቪድ ፕሮቶኮል ምክንያት ከጥቂት ጨዋታዎች በቀር በአመዛኙ ጨዋታዎች ከ10 ያልበለጠ ተመልካች ወደ ስታዲየም ሲገባ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በቀጣዩ የውድድር ዓመት ግን ስታዲየሙ ከሚይዘው የተመልካች መጠን 1/4ኛው (25%) ፕሮቶኮሉን በጠበቀ መልኩ እንዲገባ ተወስኗል።

በየጨዋታው ባለሜዳ የሚሆነው ክለብ ከሚፈቀደው የተመልካች መጠን 70% የሚያስገባ ሲሆን ከሜዳ ውጪ የሚሆነው ክለብ 30% ደጋፊዎቹን እንዲያስገባ ይፈቀድለታል። ከሚገኘው ገቢም 10% ለስታዲየሙ ባለቤት፣ 80% ባለሜዳ ሆኖ ለሚጫወተው ክለብ እንዲሁም 10% ለአክሲዮን ማኅበሩ የሚከፋፈል ይሆናል።

ትኬት እና ተመልካች የሚስተናገድበትን ሒደት ባለሜዳው እንዲቆጣጠር በማኅበሩ አማካኝነት ሀሳብ የቀረበ ቢሆንም በጉባዔተኛው በኩል ጨዋታዎች በአንድ ቦታ የሚካሄዱ ሆነው ሳለ እያንዳንዱ ክለብ ይህን ሒደት እንዲቆጣጠር ማድረግ ለአሠራር አመቺ የማይሆን በመሆኑ ለሌላ አካል ይሰጥ (Outsource ይደረግ)፣ ከከተማው ርቆ ከሄደ በኋላ ትኬት አጥቶ እንዳይመለስ በኦንላይን ትኬት ይሸጥ፣ ሒደቱን ማኅበሩ ይቆጣጠር እና ሌሎች ሀሳቦች ተነስተውበት በሒደት ታይቶ እንዲወሰን አቅጣጫ ተሰጥቶበታል።

የክፍያ መጠኑን በተመለከተ በማኅበሩ የቀረበው ምክረ ሐሳብ በሁሉም ስታዲየሞች ተመሳሳይ የክፍያ ሥርዓት እንዲኖር ተደርጎ በደረጃ በመከፋፈል አንደኛ ደረጃ 300 ብር፣ ሁለተኛ ደረጃ 200 ብር፣ ሦስተኛ ደረጃ 100 ብር፣ እንዲሁም አራተኛ ደረጃ 50 ብር እንዲሆን ሀሳብ ቀርቧል። ሆኖም ከጉባዔተኛው የተለያዩ የክፍያ መጠን ሀሳቦች በመቅረባቸው በቀጣይ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሏል።

ሌላው ጥያቄ የተነሳበት ጉዳይ በተቀራራቢ ሰዓት የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ስታዲየም የሚገቡ ተመልካቾች ሁለቱንም ጨዋታ ይመለከታሉ ወይስ አንዱን ተመልክተው ለቀጣዩ ጨዋታ ትኬት ለቆረጠው ተመልካች በመልቀቅ ሌሎች ተመልካቾች እንዲገቡ ይደረጋሉ የሚል ነው። በመጀመርያ የገቡትገወጥተው ሁለተኛ ጨዋታ ላይ የሚታደሙት እንዲገቡ ይደረግ ከተባለስ ሁለተኛው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ይህን ሒደት እንዴት ማስኬድ ይቻላል የሚለው ጥያቄ ተነስቶበታል። ከላይ እንደተጠቀሱት ሁሉ ማኅበሩ ይህ ጉዳይ ላይ በቀጣይ ተወያይቶ እንዲወስን አቅጣጫ ተሰጥቷል።