ሀድያ ሆሳዕና አዲስ ረዳት አሰልጣኞችን ሾሟል

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረት በሀድያ ሆሳዕና በረዳት አሰልጣኝነት አብረዋቸው የሚሰሩ ሦስት ባለሙያዎችን አሳውቀዋል፡፡

በ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈው ሀድያ ሆሳዕና ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከተለያየ በኋላ በምትኩ ሙሉጌታ ምኅረትን በቦታው መተካቱ ይታወሳል፡፡ ለ2014 የውድድር ዘመን በሆሳዕና ከተማ መቀመጫውን በማድረግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኘው ክለቡ ከዋና አሰልጣኙ በተጨማሪ ረዳት አሰልጣኞች ያስፈልጉት ስለነበር በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረት አቅራቢነት ሶስት የአሰልጣኝ ቡድን አባላት በአንድ ዓመት ስምምነት መቀላቀላቸውን የክለቡ ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ያሬድ ገመቹ የአሰልጣኝ ሙሉጌታ የመጀመሪያው ረዳት አሰልጣኝ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ፣ ስልጤ ወራቤ ፣ ኢኮሥኮ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ያገለገለው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ከ2011 ጀምሮ ደግሞ በሲዳማ ቡና የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ረዳት በመሆን እስከ ተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ድረስ በክለቡ ቆይታን አድርጓል፡፡ ከአሰልጣኝነቱ በፊት በተጫዋችነት እና በእግር ኳስ ዳኝነት ያገለገለው የስፖርት ሳይንስ የማስተርስ ተመራቂው ያሬድ ገመቹ በ2014 የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ረዳት በመሆን ወደ ሀድያ ሆሳዕና ተጉዟል፡፡

ሁለተኛው የቡድኑ ረዳት በመሆን ሆሳዕና የደረሰው መቅድም ገብረህይወት ነው፡፡ የቀድሞው የሰበታ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑን ካገባደደ በኋላ ወደ አሰልጣኝነቱ ሙያ ጎራ በማለት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ደግሞ በአሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ በሚሰለጥነው ወልድያ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ ሀድያ ሆሳዕና በማምራት የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ሁለተኛው ረዳት አሰልጣኝ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ሦስተኛው ረዳት ወይንም በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት የተሾመው ደግሞ ቅዱስ ዘሪሁን ሆኗል፡፡ የቀድሞው የአርሲ ነገሌ እና ደቡብ ፖሊስ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የነበረው ቅዱስ ወደ አሰልጣኝነቱ ከገባ በኋላ በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት ፕሮጀክቶችን በመያዝ ሲያሰለጥን የሚታወቅ ሲሆን ከ2012 ጀምሮ ደግሞ የሀዋሳ ከተማ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን ከክለቡ ጋር ቆይቶ በሀዋሳ አብረው መስራት የቻለውን የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሆሳዕና አምርቷል፡፡