ሀዋሳ ከተማ የቀድሞው ሁለት ተጫዋቾቹን ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኝ አድርጎ ሲሾም የብርሀኑ ወርቁ ውልም ለተጨማሪ ዓመት ተራዝሟል፡፡
ብርሀኑ ወርቁ ውሉ ተራዝሞለታል። የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ከ2010 ጀምሮ የክለቡን ከ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድኖች ሲያሰለጥን የቆየ ሲሆን ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ የዋናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል በክለቡ ያለው አሰልጣኙ ተጨማሪ አንድ ዓመት አራዝሟል።
አዲስ የክለቡ ተጨማሪ ሁለተኛ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጥሪ የደረሰው የቀድሞው ጠንካራ ተከላካይ ገረሱ ሸመና ነው፡፡ እግር ኳስን ከሃያ ዓመታት በላይ የተጫወተው ገረሱ ከ1987 እስከ 1993 በሀዋሳ ከተማ የተጫዋችነት ዘመኑን የጀመረ ሲሆን በመቀጠል ለትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ኒያላ ፣ ሜታ ቢራ ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ወራቤ እስከ 2009 ድረስ የረዘመ የተጫዋችነት ዘመኑን አሳልፏል፡፡ ከእግር ኳሱ ከተገለለ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት ሙያው ጎራ በማለት ያለፉትን አራት ዓመታት የስልጤ ወራቤ ረዳት አሰልጣኝ እና በአንደኛ ሊጉ ቡሌሆራ ከተማ ደግሞ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሲሰራ ቆይቶ የሀዋሳ የአሰልጣኞች ቡድን በሁለት ዓመት ኮንትራት ተቀላቅሏል፡፡
ሦስተኛ ረዳት ወይንም የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን በሁለት ዓመት ውል ሀዋሳን የተቀላቀለው አዳሙ ኑሞሮ ሆኗል፡፡በመብራት ሀይል ታዳጊ ቡድን ከተገኘ በኋላ ከ1990 እስከ 1993 ሀዋሳ ከተማን በግብ ጠባቂነት በማገልገል የክለብ ህይወትን የጀመረው አዳሙ በመቀጠል ወደ ልጅነት ክለቡ መብራት ሀይል ተመልሶ ከተጫወተ በኋላ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ሙገር ሲሚንቶ ፣ መከላከያ እና ኢትዮጵያ መድን ተጫውቷል። በዳሽን ቢራ ተጫዋች እና አሰልጣኝ በመሆን ወደ ስልጠናው ዓለም ከገባ በኋላ በመቀጠል ወደ ሰበታ አምርቶ እስከ ተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ድረስ በክለቡ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሆኖ አሳልፎ ወደ ሀዋሳ ከተማ ከረጅም ዓመት በኋላ ተመልሷል፡፡