የዩጋንዳ አቻውን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን አሰላለፍ ሶከር ኢትዮጵያ ከጨዋታው ሰዓታት በፊት አግኝታለች።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቀጣዩ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከቀናት በኋላ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ይታወቃል። ታዲያ ለእነዚህ ጨዋታዎች ዝግጅቱን ሲያደርግ የከረመው ቡድኑም ሀሙስ ከሴራሊዮን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጎ ያለ ግብ አቻ የተለያየ ሲሆን ዛሬ ዘጠኝ ሰዓት ደግሞ በአሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ከሚመራው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያከናውናል።
አሠልጣኝ ውበቱ እና ረዳቶቻቸው ከሀሙሱ የሴራሊዮን ጨዋታም 9 ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ታውቋል። በዚህም አቻ በተጠናቀቀው ጨዋታ የተሰለፉት ተክለማርያም ሻንቆ፣ ረመዳን የሱፍ፣ አስቻለው ታመነ፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ይሁን እንደሻው፣ ታፈሰ ሠለሞን፣ መስዑድ መሐመድ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሽመክት ጉግሳ አርፈው ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ አስራት ቱንጆ፣ ምኞት ደበበ፣ ያሬድ ባዬ፣ ደስታ ዩሐንስ፣ ጋቶች ፓኖም፣ በዛብህ መለዮ፣ ሽመልስ በቀለ፣ አቡበከር ናስር፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና አቤል ያለው የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ገብተው ጨዋታውን የሚጀምሩ ይሆናል።