ዋልያዎቹ ከከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ጋር ዩጋንዳን አሸንፈዋል

የዩጋንዳ አቻውን በአቋም መፈተሻ ጨዋታ የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ጋር ድል ተቀዳጅቷል።

ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከሰዓትበባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከዩጋንዳ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጓል። ሀሙስ ከሴራሊዮን ጋር ተጫውቶ አቻ የተለያየው ቡድኑም ያለ ግብ ከተጠናቀቀው ጨዋታ ዘጠኝ ተጫዋቾችን ለውጦ ወደ ሜዳ ገብቷል። በዚህም ተክለማርያም ሻንቆ፣ ረመዳን የሱፍ፣ አስቻለው ታመነ፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ይሁን እንደሻው፣ ታፈሰ ሠለሞን፣ መስዑድ መሐመድ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሽመክት ጉግሳ እንዲያርፉ ተደርጎ ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ አስራት ቱንጆ፣ ምኞት ደበበ፣ ያሬድ ባዬ፣ ደስታ ዮሐንስ፣ ጋቶች ፓኖም፣ በዛብህ መለዮ፣ ሽመልስ በቀለ፣ አቡበከር ናስር፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና አቤል ያለው ጨዋታውን እንዲጀምሩ ሆኗል።

ያለ ተመልካች የተከናወነው የሁለቱ ቡድኖችን ጨዋታ ለመከታተል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር፣ ም/ኮሚሽነር ዱቤ ጅሎ እና የእግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በስታዲየሙ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

ገና ከጅማሮ የዩጋንዳ የግብ ክልል መፈተሽ የጀመረው ዋልያው በጊዜ መሪ ለመሆን በአምበሉ ሽመልስ በቀለ አማካኝነት የሰላ ጥቃት ፈፅሞ ነበር። ከዚህ የከሸፈው ሙከራ በኋላም ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾች ጨዋታው ገና ሩብ ሰዓት ሳይሞላው በ11ኛው ደቂቃ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም አቡበከር ናስር ከሽመልስ በቀለ የደረሰውን ድንቅ ኳስ በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ግብነት ቀይሮት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መምራት ጀምሯል። የግቡ ባለቤት አቡበከር ከሰባት ደቂቃዎች በኋላም ደስታ ዮሐንስ ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ አስቆጥሮት የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ በሚል ጎሉ ተሽሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን የኳስ ቅብብል ማቋረጥ ቀላል ያልሆነላቸው ዩጋንዳዎች ሙሉ ለሙሉ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው መጫወትን መርጠዋል። ይህ አጨዋወት ይበልጥ የጠቀመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ አስጨንቆ መንቀሳቀሱን ቀጥሎበታል። 24ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አስራት ቱንጆ ከመስመር አሻምቶት ተከላካዮች ወደ ውጪ ያወጡት ኳስ ከመዓዘን ሲሻማ ተስፈንጥሮ የደረሰው ያሬድ ባዬ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መንቀሳቀስ የቀጠሉት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በ36ኛው ደቂቃ አማኑኤል ከቀኝ መስመር ከተከላካይ ጋር ታግሎ ወደ ሳጥን ባሻገረውን እና የግቡ ባለቤት አቡበከር ወደ ግብነት ለመቀየር በጣረው አጋጣሚ ሌላ ግብ ሊያገኙ ነበር። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ጥሩ የእርስ በእርስ መናበብ የታየባቸው አማኑኤል እና አቡበከር አስደንጋጭ ጥቃት ፈፅመው ነበር። ነገርግን አቡበከር የሞከረው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል።

አንድም ዒላማውን የጠበቀም ሆነ ያልጠበቀ ሙከራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ በመጀመሪያ አጋማሽ ያላደረጉት ዩጋንዳዎች የበዛ ግብ ላለማስተናገድ ሲታትሩ ታይቷል። በ41ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አቤል ያለው ከሽመልስ የደረሰውን ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ በሞከረው ኳስ የሚመሩበት የግብ ብዛት ሊሰፋ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድ ለምንም መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ብልጫቸውን ያስቀጠሉት ዋልያዎቹ በ54ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም አቤል ተቀይሮ ከገባው ሽመክት ጉግሳ የተቀበለውን ኳስ የግቡን ቋሚ አስነክቶ መረብ ላይ ቀላቅሎታል። ይህ ግብ ከተቆጠረ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ዩጋንዳዎች በጨዋታው ተስፋ የሰነቁበት የሚመስለውን ጎል አግኝተዋል። በዚህም ተቀይሮ የገባው የኑስ ሴንታሙ ከወደ ቀኝ ካዘነበለ ቦታ ያገኘውን የርቀት ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶት የግብ ዘቡ ፋሲል ገብረማርያም መረብ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ቢያስተናግዱም ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የታዩት ዋልያዎቹ በ60ኛው ደቂቃ ሽመክት የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ቻርለስ ሉኩዋጎ በመታው ኳስ ዩጋንዳን ዳግም አስደንግጠዋል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም ጋቶች ፓኖም ከቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ሞክሮት ነበር።

ተከታታይ የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ከእጃቸው የወጣውን ብልጫ ለማግኘት የጣሩት አሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮችን በማድረግ አቻ ለመሆን ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ጨዋታው 70ኛው ደቂቃ ላይ ደርሷል። በዚህ ደቂቃ ላይ ደግሞ ሽመክት በድጋሚ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግብ ዘቡ ቻርለስ ሉክዋጎ ሲመልሰው በጥሩ አቋቋም ላይ በመሆኑ ያገኘው አቤል በግንባሩ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ግብ ሊያስቆጥር ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያላቸውን አቅም ተጠቅመው ለመጫወት የሞከሩት ዩጋንዳዎች በ80ኛው ደቂቃ ባገኙት የመዓዘን ምት ኳስ እና መረብን ሊያገናኙ ነበር። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ በ88ኛው ደቂቃ ምኞት የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ባገኙት የቅጣት ምት የጠራ ጥቃት ፈፅመዋል። በዚህም ጆሴፍ ቤንሰን ኦቻያ በጥሩ ሁኔታ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፋሲል እና የግቡ ቋሚ ተባብረው አምክነውታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።ያጋሩ